ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ ክፍል አንድ

ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት
እና
የባለሙያዎች ማብራሪያ

ክፍል አንድ

የሄኖክ ስብስብ
ታህሳስ 2005ዓ.ም
{PDF}
ውድ አንባቢዎች፤ ከዚህ በታች የምታነቡት ሀሳብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ላይ የተነበቡ ሲሆን ምንጫቸውም ከየመጣጥፎቹ ግርጌ ይገኛል፡፡ ለዚህም ነው “ስብስብ” በሚል ለመግለፅ የተገደድኩት፡፡ በስብስብ መጣጥፎቹ ላይ የጨመርኩት አንዳች ነገር የለም፤ ምክንያቱም አላማዬ በሞክሼ ፊደላት እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ ለመበየን ሳይሆን፣ እንደኔው ግራ ለተጋቡት ማጋራት ነውና፡፡
-1-
የፊደል ዘር ይጠበቅ ባህሉም ይከበር
በፊታውራሪ አበበ ሥዩም ደስታ

በፊደሎቻችን ላይ ሦስት ሀ – ሐ – ኀ፣ ሁለት አ – ዐ -፣ ሁለት ሠ – ሰ ሁለት፣ ጸ – ፀ አሉ፡፡ እነዚህ ፊደሎች የራሳቸው የሆነ የስም አጠራርም አላቸው፤ ሀሌታው ሀ፣ ሐመሩ ሐ፣ ብዙኃን ኀ፣ ንጉሡ ሠ፣ እሳቱ ሰ፣ ጸሎት ጸ፣ ፀሐዩ ፀ ይባላሉ፡፡ በጽሑፍ የሚገቡበትን ተገቢ (ተስማሚ) ቦታም አላቸው፡፡ ለምሳሌ በሁለት ፊደሎች መጠቀም ይቻላል፡፡ ሀገር አገር ይህ ትክክለኛ አጻጻፍ ሲሆን፤ ነገር ግን ከዚህ ውጪ ሐገር፣ ኀገር ብሎ መጻፍ ግን ስሕተት ይሆናል፤ የሚከተሉትን ደግሞ እንመልከት፤

ሕገ መንግሥት፣ ሕገ ወጥ፣ ሕዝብ፣ ሕብረት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ወዘተ. የመሳሰሉት አጻጻፋቸው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ልማዳዊ አሠራር ውጪ ህገ መንግሥት፤ ህገወጥ፤ ህዝብ፤ ህብረት፤ አቃቤ ህግ ስሕተታዊ አጻጻፍ ይሆናል፤ ሌላ ማስረጃ ቢፈለግ፤ ኃይለሥላሴ የሚለው ስም ሦስት የተለያዩ ፊደሎች ይዟል፡፡ የመጀመርያው ፊደል ብዙኀን – ኃ – ሲሆን፣ ከንጉሡ -ሥ- ሳድስ፣ ከእሳቱ -ስ- ሃምስን በመጻፍ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ሀይለ ስላሴ ብሎ ቢጻፍ ግን የፊደሎቻችን የአጻጻፍ ሥርዓት ማፋለስ ይሆናል፤ በአቦ ሰጡኝ ፊደሎቻችን አለቦታቸው መግባትም፣ መጻፍም የለባቸውም፡፡

በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩት የተከበሩ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ የቅድሚያ ዓይነተኛ ሥራቸው የፊደሎች ዘሮች አለቦታቸው እንዳይጻፉ መጠበቅ ነበር፤ በዚያን ወቅት ተማሪ ሁኜ አልፎ አልፎ በጋዜጣ እንዲወጣልኝ አንድ አንድ ሐሳብ በማመንጨት እጽፍ ስለነበር ብዙ ጊዜ አርመውኛል፡፡

ከእሳቸው በተማርኩት ትምህርትና ባገኘሁት ልምድ አእምሮዬን አሻሽያለሁ፡፡ በቀድሞው የንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ ሥርዓት የክፍል ሹም የመጀመርያ ሹመት ሆኖ ወደ ላይ እንደሚከተለው ይዘልቃል፡፡ ዲሬክተር ዋና ዲሬክተር፤ ረዳት ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዲ-ኤታ፤ ሚኒስትር፡፡ ከምክትል ሚኒስትር ወደ ላይ ያሉት እስከ ሚኒስትር ማዕረግ የደረሱት ክቡር ይባላሉ፡፡ ከዚህ በታች ያሉትን ግን ክቡር አይባሉም፡፡ በተመሳሳይ ያሉትን ማለት ኮሚሽነሮች፤ ሌ/ጀኔራሎች፣ አምባሳደሮች ክቡር ይባላሉ፡፡ ሚኒስትሮች የነበሩ በዳሬክተርና በሥራ አስኪያጅነት ሥራ ቢመደቡ እንኳን የቀድሞውን የሚኒስትር ማዕረጋቸውና ክብራቸው አይቀነስባቸውም፡፡ ክቡር መባል አለባቸው፡፡ ሥርዓት ነውና፡፡ ይህንኑ መለመድ ይገባዋል፤ በወታደሩ ሹመት አሰጣጥ ግን ያለው ሥርዓት የተጠበቀ ስለሆነ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ከዚሁ ሌላ የምለው አለኝ፡፡ ባሁኑ በኢሕአዴግ መንግሥት ዘመን አምባሳደር ነዋሪ የማዕረግ መጠሪያ ስም ሆኖአል፡፡ አንድ አምባሳደር የዲፕሎማሲውን ሥራ አቁሞ ሲዛወር ልክ በሥራው እንዳለ ተቆጥሮ “አምባሳደር” እየተባለ መጠራት የለበትም፡፡

ለምሳሌ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አምባሳደርነት ተሹመው የነበሩት ክቡር አቶ ጋሻው ዘለቀ፣ ክቡር አቶ ዘነበ ኃይለ፣ ክቡር ልጅ መንበረ ያየህ ይራድ፤ ክቡር ፊታውራሪ መሐመድ ሲራጅ ብዙ ዘመን በአምባሳደርነት ሲሠሩ ቆይተው ተልእኮዋቸውን ፈጽመው ወደ አገራቸው ሲመለሱ አምባሳደር የሚል ቀርቶ በቀድሞ ስማቸው አቶ ተብለው ነበር የሚጠሩት፤ ይህንኑ ጠይቆ ለማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ፊታውራሪ የነበሩትም፤ ፊታውራሪ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዘላቂ ሆኖ ከሰው ጋር ቅጽል የማዕረግ ስም ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ በራሴ ምሳሌ ልውሰድ፤ ከግርማዊ ጃንሆይ በአዋጅ የተሰጠኝ የማዕረግ ስም ፊታውራሪ ነው፤ በዚህ ምድራዊው ዓለም እስካለሁ ድረስ የምጠራበት ሲሆን፣ ከሞትኩም በኋላ እጠራበታለሁ፡፡ እንዲሁም በንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድ የሚሰጠው የሥልጣንና ማዕረግ ተዋረድ ባላምባራስ፣ ግራዝማች፣ ቀኛዝማች ፊታውራሪ፣ ደጀዝማች፣ ቢትወደድ፣ ራስ ቢትወደድ፣ ልዑል ራስ፣ አልጋ ወራሽ፣ ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብላታ፣ ብላቴን ጌታ፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ፣ ሊቀ መኳስ በሕይወት ሳሉ ይጠሩበታል፡፡ ከሞቱም በኋላ ስማቸውና ታሪካቸው በተነሣ ቁጥር ከመቃብር በላይ ሆኖ በማዕረጉ ስም ይጠሩበታል፡፡

አምባሳደር ግን የማዕረግ ስም መጠሪያ ስላልሆነ የዲፕሎማሲ ሥራቸውን ሲያቋርጡ አምባሳደር ተብለው ሊጠሩበት አይገባም፡፡ በሌላ መንግሥት የማይሠራበት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ለብቻው በዚህ ስም አጠራር ሕጋዊ ማድረጉ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ እንደ ማዕረግ በዘላቂነት ይጠሩበት ከተባለ እኔ ከማሳሰብ በቀር እምጎዳበት የለም፡፡ ከዚህ ጋር የማያይዘው ሌላም አለ፤ ከላይ በዝርዝር እንደገለጽኩት ባሁኑ ሰዓት ዲሬክተር ጄኔራል እየተባሉ አንዳንድ ሹማምንት ይጠሩበታል፡፡ በእኔ አስተያየት ዲሬክተር ጄኔራል ከማለት ይልቅ ዋና ዲሬክተር ቢባሉ ወይም ለስም አጠራሩ የሚቀል ስለሆነ ረዳት ሚኒስትር እየተባሉ ቢጠሩ መልካም ነው፡፡ በዚህ ቢታረም ያማረ ይሆናል፡፡

በማጠቃለያ የማቀርበው ሐሳብ በየዕለቱ እና በየሳምንቱ በሚታተሙ ጋዜጦች መጽሔቶች፣ መጻሕፍት የፊደሎቻችን ዘሮችና ልማዳዊ የአጻጻፍ ሥርዓቶች ይጠብቁ (ይከበሩ) በማለት ሐሳቤን እቋጫለሁ፡፡ እንዲሁም የኮምፒውተር ፀሐፊዎች ይህንኑ የአጻጻፍ ስልት (ፈለግ) ተከትለው ይጠቀሙበት በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ በተጨማሪም ደራስያን፣ አስተማሪዎች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ ከያኒያን ይህንኑ እንዲተገብሩ ማድረግ የግል ኃላፊነት ስላለባቸው ትኩረት ይስጡበት እላለሁ፡፡

ሌላው መታረም የሚገባው፣ “ስፖርት” እየተባለ የሚጻፈው ነው፡፡ ምክንያቱም የአውሮፓ ፊደል ኤስ (S) የእ ፊደል ድምፅ ስላለው፣ Sport ቢጻፍ ትክክል ነው፤ የእኛው ፊደል (ስ) ግን ድምፁ የተዋጠ ስለሆነ እ ፊደል ተጨምሮበት “እስፖርት” ቢባል የተሻለ ነው፤ እንዲሁም ለርምጃ እርምጃ ቢባል፣ በኔ በኩል ጥሩ ስለሆነ ታስቦበት ቢታረም መልካም ይመስለኛል፡፡
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ

-2-
የሐበሻ ፊደላት ለውጥ ያስፈልጋቸዋል?

በተመስገን ታ

በአገራችን ሚዲያዎች ፊደሎቻችን ማሻሻያ ይደረግባቸው፣ አይ አይደረግባቸውም፡፡ ማሻሻያ ማድረግ ቢያስፈልግስ መብቱ የማነው? በሚሉ ጉዳዮች ጐራ ተለይቶ ክርክሩ ጦፏል፡፡ እኔም እንደ ዜጋ ጥያቄው አጫረብኝ፡፡ የሐበሻ ፊደላት ለውጥ ያስፈልጋቸዋል? የሚል፡፡ እርግጥ ነው፡፡ የፊደላቱን ምልክት ከማወቅ ባለፈ ብዙዎቻችን የምልክት አሰያየሙን ሥረ መሠረት አናውቅም፡፡

በዚህም የተነሣ በሞክሼ ፊደላት አጠቃቀማችን ላይ ጽሑፋችን ሁሉ ዝብርቅርቅ ነው፡፡ ይህንንም ጽሑፍ ስጽፍ ይኼው የሞክሼ ፊደላት ሰፊ አማራጭነት በሰጠኝ ነፃነት አንድን ቃል በተለያዩ የሞክሼ ፊደላት እጽፈዋለሁ፡፡ እነዚህ ሞክሼ ፊደላት እንደ አማራጭ የምንጠቀምባቸው ሰፊ ነፃነት ያጐናፀፉን አድርገን ከመውሰድ ባለፈ የትርጉም መዛባት ወይም በአጠቃቀም መዘበራረቅ ሥነ ጽሑፉን ጥላ ያጠላንበት መስሎ አይታየንም፡፡ የትርጉም መዛባት ስለማምጣት አለማምጣቱም ሆነ የተዘበራረቀ አጠቃቀማችን ችግር ያስከተለ ስለመሆኑ ፊደሎችን ለመለየት ስንማርም ሆነ ከዚያ ባለፈ ያገኘነው ተዛማጅ ትምህርት ስለሌለ ፊደሎችን በምንጠቀም ሰዎች የምንወቅስበት አንድም አግባብ የለም፡፡ ታዲያ ተወቃሹ ማን ይሁን ሲባል የፊደላቱ ባለቤት፣ ቋንቋን የሚያስተምሩና ብሔራዊ ቋንቋዬ ነው ያለው መንግሥት እንጂ፡፡

የአማርኛ ፊደሎቻችን የራሳቸው ፊደላት ካሏቸው አገሮች ጋር በእኩል የሚመደቡን በመሆናቸው ከክብር አንፃር ክብርና ኩራት የሚያሰጡ ሲሆን፣ ከታሪክ አንፃር ደግሞ ታሪካዊ ናቸውና በቅርስነትም የሚታዩ ሊሆን ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ የተንጋደደ አስተያየት የምንይዝ ሰዎች ቅርስ በዩኔስኮ ዕውቅና ካላገኘ በስተቀር ቅርስነቱን ዝቅ አድርጐ ወይም አነስተኛ የቅርስነት አመለካከት እንዳለው የመገመት አባዜ ያለብን አለን፡፡ ይህ አመለካከት ሙሉ በሙሉ ከሥሩ ተነቅሎ መጥፋት ይኖርበታል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ቀደምት አባቶች የኛ የሆኑ ፊደላትን ሲቀርፁ ከአነጋገር ጋር በተያያዘና ቃል መሥርተው በሚፈጥሩት ድምፅ አዝለውት የሚመጡት የመግባቢያ ትርጓሜ ጥልቀት ባለው መልኩ ፈትሸውት ያስቀመጡት ነውና ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን ፈላስፎቻችንን የምናደንቅበትና ክብር የምንሰጥበት ቅርሶች ናቸው፡፡ በእርግጥ ቁጥሮቻችንና ፊደሎቻችንን የፈለሰፉ ኢትዮጵያ ፈላስፎቻችን የፈጠሩትን ፊደል ተጠቅመው እራሳቸውን እነማን እንደነበሩ እንደ አውሮፓውያኑ፣ ላቲኖቹ፣ እስያውያኑ፣ ወዘተ መዝግበው ለትውልድ ባለማስተላለፋቸው በስማቸው እያነሳን ስናሞግሳቸው እንዳንኖር ሆነዋል፡፡ ዳሩ ግን በአገራችን እንደቱፊት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃልም አለ፡፡ ‘ስለ አንተ ምላስህ ሳትሆን ሥራህ ይመስክር’ የሚለው የአገራችን ሃይማኖታዊ ቱፊቶች እንደነበሩ ተጠብቀው በቅብብሎሽ አሁን ላይ በመድረሳቸው በእምነቱም ቢሆን ከዓለም ሃይማኖቶች በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ሆነን እዚህ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ነብዩ ሙሴ የተወለደባት ግብፅ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት እሥራኤል ያልጠበቁትን ሃይማኖታዊ ቱፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠብቆ ከልጅ ልጅ እየተሸጋገረ አሁን ካለንበት ደርሷል፡፡

ምናልባትም ፊደሎቻችንን የፈጠሩትም ይሁኑ በተለያዩ ጊዜያት ያሻሻሉትም ጭምር በዚሁ መንሳዊ ቱፊት መነሻነት ሊሆን ይችላል፡፡ ስማቸው በክብር ተመዝግቦ ለትውልድ ያልተሸጋገረው፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚሀን ፊደላት የፈለሰፉ ፈላስፎቻችን ስማቸውን በክብር መዝገብ ያኖሩ ቢሆንም ይህ የክብር መዝገብ በአግባቡ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሆኖ ባለመቀመጡ ምክንያት በመጥፋቱ ወይም በመበላሸቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች እስካሁን የሚሰበሰቡት በቤተ ክርስቲያን በመሆናቸው ቤት ክርስቲያኖቻችንን ባለቡት ሁሉ የማወቅና በሙዚየምነት የያዟቸውን የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች በዝርዝር አለመታወቁ ምክንያት ወደ ሕዝብ እውቀት ስላልመጡ ሊሆን ይችላል፡፡

አገራችን በተለያዩ ጊዜያት በውጭ አገሮች ስውርና ቀጥተኛ የታሪክ መዛግብትን ዝርፊያና ድምጥማጣቸውን የማጥፋት ሴራ እንዲሁም በአገር ውስጥም ቢሆን በየጊዜው ይካሔድ በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ከግንዛቤ ማነስ የቤተ መዘክር ታሪኮቻችን ይወድሙ እንደነበር በአፈታሪክም ቢሆን የሚነገሩ አሉ፡፡ እናም በነዚህ ሁኔታዎች የነዚህ የፈላስፎቻችን ታሪክ ጠፍተው ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ የቤተ ክህነትን ዜማና አቋቋም የፈለሰፈው ቅዱስ ያሬድ ታሪክ እዚህኛው ትውልድ የደረሰው ታሪኩ ተመዝግቦ ሳይጠፋ ከትውልድ ወደ ትውልድ በመተላለፉ ነው፡፡ በመሆኑም ቁጥሮቻችንና ፊደሎቻችንን የፈጠሩትም ሆኑ ያሻሻሉት ፈላስፎች ለምን በስም ሊታወቁ አልቻሉም?

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም ትክክለኛ ባልሆነ የውጭ የተሳሳተ አስተሳሰብ ተፅዕኖ ታሪክን ወደ ውጮች ለመወርወር የሚታሰብበት አጋጣሚ ይታያል፡፡ ይህም በመሆኑ የኛነት መገለጫ የሆኑትን ፊደላትም የውጭ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላል ብለን የምናስብ ኢትዮጵያዊ ትውልዶች እንዳንኖር እሰጋለሁ፡፡ ከድምፅ አወጣጥ ጋር አስተሳስሮ ለሚፈጠረው ድምፅ ምን ዓይነት የፊደል ምልክት ይኑረው ብሎ በማሰብ ምልክቱን ማስቀመጥ ቋንቋው የአፍ መፍቻው ካልሆነ እንዴት አስቸጋሪ እንደሚሆን ምንም ሌላ ማረጋገጫ የለውም፤ በአፍ መፍቻ ቋንቋችን በየራሳችን የምናውቀው ነውና፡፡ ለምሳሌ ያህል በጥቂቱ ለመጥቀስ የኦሮምኛው፣ የአማርኛውና የወላይተኛው የአነጋገር ዘይቤ ልዩነቶችን በተወሰኑት ቃላት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የትግርኛ ቋንቋ በትናጋ የሚናገረውን አማርኛው በከንፈሩ ሊናገረው ይችላል፡፡ በኦሮምኛ ላልቶ የሚነገረው በአማርኛው ከሮና ጠንክሮ በማጥበቅ ሊነገር ይችላል፡፡ በወላይተኛው ቃሉ የሌለ ይሆንና ሊጣመም ይችላል፡፡ ለአብነት ያክል ቢዳዳ፣ መቀሌ፣ ፈረስ፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ከነዚህ እውነታዎች መነሻነት የአማርኛ ፊደሎቻችንን የፈለሰፉ ፈላስፎች ወይም ያሻሻሉት ሰዎች ቋንቋው የአፍ መፍቻቸው ሊሆን እንደሚችል በዋናነት መገመት ይቻላል፡፡

የሐበሻ ፊደላትንና ቁጥራትን እነማን ፈጠሯቸው? የሚለውን ጥያቄ ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምንጠቀምባቸውም መግለጫ ወይም አንድምታ አብሮ ለትውልድ ባለመተላለፉ አሁነኛው ትውልድ ላይ ግር የማለት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ እያንዳንዱ ፊደል ተጣምሮ ከሚሰጠው ትርጓሜ አንፃር የድምፅም ሆነ የፊደሉ ተጠሪነት የየራሳቸው አግባብነት አላቸው፡፡ እነዚህን የፊደል አግባብነትና የሚወክሉትን ድምፅ ጭምር እንዴት? መቼ? እና ለምን? መጠቀም እንዳለብን የፊደላት አጠቃቀም አንድምታ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ይህም በመሆኑ ሞክሼ ፊደላትም ሆኑ በአንድ ፊደል ስረ ግንድ የሚነበቡ ተመሳሳይ ድምፆች የፊደሎቹ ዘሮች ያለአስፈላጊ እየመሰሉ የመታየት እንዲሁም መሻሻል አለባቸው የሚል አስተሳሰብ እየገነነ እየመጣ ነው፡፡ ለማጥፋትም የሚያኮበኩቡ ከዚህም ባለፈ የሚዝቱ ‹‹ምሁራን›› እየታዩ ነው፡፡ ምሁር ማለት ፈላስፋ ማለት አይደለምና ግራ ቢገባቸው አይገርምም፡፡ ብዙዎቻችን ለያዝነው የትምህርት ደረጃ በተሰጠን የዕውቅና ወረቀት ላይ ብቻ ተንጠላጥለን ሥራችን ሳይሆን ልባችን በትቢት ይወጠራልና፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሥልጠና ላይ አሠልጣኙ የንድፈ ሐሳባውያንን ቱሩፋት እንዲህ በማለት ነገረን፡፡ ‹‹አንድ ወላጅ ልጃቸው ሁልጊዜ ፈተና ይደፍናል፡፡

ሁሌም አንደኛ ይወጣል፡፡ በዚህ ችሎታው የሚደሰት ልጅ ፈተና የመድፈኑንና አንደኛ የመውጣቱን ዜና ለአባቱ ሲናገር አባት አይሞቃቸውም ወይም አይበርዳቸውም፡፡ የሚደሰቱም የሚከፉም አይሆኑም፡፡ ልጅ ታዲያ የሚጠብቀው የአባቱን እጅግ አድርጐ መደሰት ነበርና ‘አባዬ ጉብዝናዬን እያየህ ለምን እጅጉን ደስ አላለህም?’ ይልና አባቱን ይጠይቃል፡፡ አባቱም በምላሹ ልጄ ሆይ ጐበዝ ነኝ የምትለኝ እኮ መምህሮችህ የነገሩህን ሁሉ በፈተናቸው መልሰህ ስለነገርካቸው ነው፡፡ እኔ ግን በጉብዝናህ የምደሰተው አዲስ ነገር ስትፈጥር ነው አሉት፡፡››

ፈላስፋ ሳይኮን ለመሆን የነበረን አጥፍቶ በዘፈቀደ አዲስ ተካን ማለት ግን ‘ምሁር’ የሚለውንም ማዕረግ ዝቅ እንዳያደርገው እሰጋለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ በፊደሎቻችን አጠቃቀም ግራ መጋባት የሁለችንም ችግር ነው፡፡ ፊደላትን ያለቦታቸው እየደነቀርናቸው ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት በስህተት ሌላ ትርጓሜ ሊይዝ እንደሚችል ይገመታል፡፡ በዚህ ሰበብም ሥነ ጽሑፎቻችን የተዛቡ እንዳይሆኑ ስጋቱ አብሮ አለ፡፡ ከዚህም ውጭ የፊደላት አጠቃቀማችን ሥርዓት ያለው ሳይሆን በዘፈቀደ በመሆኑ የምርጫ ነፃነት ቢኖረንም ዳሩ ግን የአተረጓጐም ለውጡ በቀጣይ ትውልድ ችግር እንዳያመጣ ያሰጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለለማጆችም ተጋኖ እንደሚቀርበው ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ግራ ሊያጋቡ ይችላሉ፡፡

ቁጥሮቻችንም ቢሆኑ በሂንዱ ዓረቢክ ቁጥሮች ቁጥጥር ሥር በመዋላቸው በመቀበሪያ ጉድጓዳቸው ጫፍ ላይ ነው ያሉት፡፡ በአገራችን ቀን መቁጠሪያዎችና በቤተ ክህነት ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም የሒሳብ ስሌት ውስጥ ገብተው ትውልድ እንዲጠቀምባቸው አልተደረገም፡፡ የስሌቱ ይቅርና ሺዎችን ቁጥሮች ወክሎ ለመጻፍ ግርታ ተፈጥሯል፡፡ የሐበሻ ቁጥሮች መሠረታዊ ምልክታቸው እስከ መቶ ብቻ በመሆኑ ከመቶ በላይ እንዴት እንደምንጠቀምባቸው የተቀመጠ ባለመኖሩ፡፡ ለዚህም እንደ አስረጂነት በእኛው የዘመን አቆጣጠር የሁለት ሺሕ ዓመተ ምሕረትን ማንሳት ይቻላል፡፡ በጊዜ መቁጠሪያ (ካላንደሮች) ላይ በዚህ ጊዜ የተጻፉትን ብናይ በቤተ ክህነት ጭምር በተለያዩ የግልና የመንግሥት መሥርያ ቤቶች የተለያዩ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን የመረጃ ሥነ መሠረቶች ወይም በጥናት የተደረሰባቸው የመግባቢያ መረጃዎች ባይኖሩም ልብ ለልብ በመተዋወቅ ወደ አንድ ወጥ የተመጣ ሆነ እንጂ፡፡

በቁጥሮቻችንም ሆነ በፊደሎቻችን ሌላው የራሳችን የኢትዮጵያውያን ችግር ደግሞ የኛ ካልሆኑት የውጭ የቁጥርና የፊደላት ምልክቶች ጋር እናነፃፀርና የኛ የሆነውን የኛነት መኩሪያችንን ሽርሽርን ለውጬ ተፅዕኖ እጅ እንሰጣለን፡፡ የኛ የሆኑትን በጥልቀት እንዲጠኑ በማድረግ ከጊዜ ለውጥ ጋር ከፍተቶች ታይተውባቸው ከሆነ ክፍተታቸውን ከመሙላት ይልቅ ተወቃሽ በማድረግ ከታሪክ ማኅደር እንዲነሱ ቢጫ ማስጠንቀቂያ እናሳያለን፡፡ የውጩ ተፅዕኖ ያደረገብን መሆኑን አዙረን ልናይ ባለመቻላችን ከዘመኑ ኪነ ብጀታ (ቴክኖሎጂ) ጋር የማይጓዙ ብለን በሐሰት መረጃ ወንጀለኛ እናደርጋቸዋለን፡፡ የኛ የታሪክና የቅርስ መገለጫ የሆኑንን የቁጥርና ፊደላት ምልክቶቻችን ከላይ እንደገለጽኩት ከመኮነን ባለፈ እንዴት እናበልጽጋቸው? ሳይሆን የሐሰት መረጃን መሠረት አድርገን እንዴት እናጥፋቸው? የማለት ያህል ይሆንብኛል፡፡

በእኛው በአገራችን እንኳን ብንወስድ የአሁኑ መቀምር (ኮምፒውተር) መተየቢየን (ታይፕራይተርን) ቦታ ከመረከቡ በፊት ከቁም ወይም የብራና ጽሑፍ ወደ መተየቢያ ነበር የተሸጋገርነው፡፡ ኦሎምፒያ መተየቢያን ወደ ገበያ ሲያወጣ ይህ የመጻፊያ መሣርያ ለትንግርት ተደንቋል፡፡ በወቅቱ ዋጋውም ሰማይ የነካ እንደነበር ታሪክ ዘክሮታል፡፡ ዳሩ ግን የኛውን የፊደላትና የቁጥር ምልክቶች አያውቅም ነበር፡፡ ይህ መተየቢያ የኛነት መገለጫ የሆኑትን ቅርሶቻችንን ፊደላትንና ቁጥሮችን በቅኝ ገዥነት ሊያደክም ለወረራ የመጣ መሆኑን የተገነዘቡ የጊዜው አገር ወዳድ ባለሙያ ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ዝም ብለው ማየት ህሊናቸው አልቀፈደላቸውም፡፡ ወረራውን በፀረ ወረራ ትግል ጀመሩ፡፡

ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ለሰላማዊ ትግላቸው ኦሎምፒያ ኦሊቬቲ ወደሚገኝበት አሜሪካ ተጉዘው የመጀመርያ የሰላም ጥይታቸውን ለኦሎምፒያ ኦሊቬቲ ተኮሱ፡፡ ይኸው ኩባንያ የኢትዮጵያን ፊደላት የሚያስተናግድ መተየቢያ እንዲያመርት ኢንጂነሩ ሲጠይቁ ልክ አሁን እንደሚባለው የተሰጣቸው የኢትዮጵያ ፊደላት ቁጥር ሁለት መቶ ሰባ በመሆኑ እጅግ የበዛ ባሕርያት (ካራክተር) አላቸው፡፡ ስለሆነም የሐበሻን ፊደላትና ቁጥሮች የያዘ መተየቢያ ላመርት አልችልም ነበር ምላሹ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ አለ፡፡ ብዙ የሆነን ነገር ማስተናገድ ትንንሾች ሲመጡ ሰፊ አማራጭ ይዞ ከመገኘት አንፃር ትንንሾችንም ማስተናገድ ቀላል ይሆናል፡፡ ግን ኦሎምፒያ ኦሊቬቲ አላደረገውም፡፡

ኢንጂነር ተረፈን ምላሹ እጅ እንዲሰጡ ወይም ከጦርነቱ እንዲሸሹ ወይም እንዲያፈገፍጉ አላደረጋቸውም፡፡ አፄ ምኒልክ ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ድል ለማድረግ ከእቴጌ ጣይቱና የጦር ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ስልት እንደነደፉት ሁሉ ኢንጂነር ተረፈም ድል የማድረጊያ ስልት ማሰላሰል ጀመሩ፡፡ ስልቱንም አገኙት፡፡ የጦርነት ስልት ለጦርነት የሚሆን ሲሆን የንግድ ስልት ደግሞ በንግዱ አካሔድ መሆን እንዳለበት ተረዱት፡፡ አደረጉትም፡፡ ኦሎምፒያ ኦሊቬቲን በንግድ የሚቀናቀነው ማነው? የሚለውን ምላሽ ማግኘት ነበር፡፡ አገኙም፡፡ ተቀናቃኙ የጀርመኑ ሲሜንሶ መሆኑን፡፡ ኢንጂነር ተረፈም የአገራቸውን ፊደል ከወረራ ለማዳን እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ወደ ጀርመኑ ሲሜንሶ ተጓዙ፡፡ ከቦታውም ደረሱ፡፡ ልክ እንደ ኦሎምፒያ ኩባንያ እንዳቀረቡት ሁሉ ለሲሜንስም የኢትዮጵያ ፊደል የያዘ መተየቢያ ሠርቶ እንዲያወጣላቸው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ሲሜንስም ጥያቄያቸውን ተቀበላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፊደላትን የያዘውን መተየቢያ ከነፈጠራ ባለቤትነት ሠርቶ አስረከባቸው፡፡

በቁጥርና ፊደል መተየቢያነት ከመቶ ዓመታት በላይ በዓለማችን ሪከርድ ያለው ይኸው መሣርያ አገልግሎቱን ለመቀምር (ኮምፒውተር) እስካስረከበበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት የኢትዮጵያን ፊደላትና ቁጥሮች ተንከባክቦ በመያዝ ዘመን ላመጣው መቀምር አስረከበ፡፡ የዘመኑ መቀምር እንደቀድሞው ኦሎምፒያ ኦሊቬቲ የአማርኛ ፊደላት ብዙ በመሆናቸው ላስተናግዳቸው አልችልም አላለም፡፡ ያለምንም ችግር እንዳሉ ተረክቧቸዋል፡፡ ተረክቦም በማገልገል ላይ ነው፡፡

የኛዎቹ ‹‹ምሁራን›› የፊደሎቻችን አስቸጋሪነት ልክ እንደ ኦሎምፒያው ኦሊቬቲ እየሆኑብን ነው፡፡ ኪነ ብጀታው (ቴክኖሎጂው) ወደ ወለደው መሣርያ እንዴት እናሳድገው ወይም እኛው እራሳችን የኛኑ ቅርሶች ሊያሳድግ በሚችል መልኩ አዲስ ኪነብጀታ እንፍጠር ሳይሆን ሌሎች የፈጠሩትን ኪነብጀታ ተረክበን የኛነት መገለጫ የሆኑንን የቁጥርና የፊደል ቅርሶቻችንን ልናጠፋ ወይም ልናደበዝዝ ላይ ታች እንታክታለን፡፡ የውጮች ኪነብጀታ የኛን ያስቸግረዋልና እናጥፋቸው ወይም እናዛባቸው በሚልም ዱለት መዶለት ጀምረዋል፡፡ መዶለቱ ከኢንተርናሽናል ፎኔቲክ አሶሴሽን (International Phonetic Association (IPA)) ጋር ከሆነ ይህንን በሌላ መስመር ማስተናገድ ነው፡፡ እኛ እኛን ከሆን መፍጨርጨር ይኖርብናል? ወይስ ሌሎችን ለመምሰል ታሪኮችንን ማጥፋት?

ዛሬ በሥነ ጽሑፍ ታሪክ ስናዛባ ነገ ደግሞ ቁሳዊ የሆኑ የታሪክና የሥልጣኔ አሻራዎቻችን የሆኑትን ቁሳዊ መገለጫዎቻችን አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲለደስ፣ የጀጐል ግንብ፣ ወዘተ ከቻለ ይኸው ትውልድ ካልሆነም ቀጣይ ትውልድ እንዲያጠፋቸው እያመቻቸን መሆናችንን የምንረዳ ስንቶች ኢትዮጵያውያን አለን? ምናልባትም የቁጥርና የፊደሎቻችንን ምልክት የፈጠሩትን ፈላስፎች ዝክረ መዝገብ ለትውልድ ተላልፎ እንዲታወቁ ያልሆኑት በዚሁ ሁኔታ ጠፍቶስ ቢሆን? አይሆንም አይባልም ሆኖ ይሆናል፡፡

በጣም የሚያስገርመኝ ደግሞ የቁጥሮችም ሆነ የፊደላቱ ባለመብት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሆና እያለ በግብታዊነት እናሻሽል ብሎ መነሳሳቱ አስገርሞት ይፈጥራል፡፡ እዚህ ላይ እናሻሽል ብለው የተነሱት ብቻ አይደሉም አስገራሚዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ብትሆን የቁጥሮችንም ሆነ ፊደላቱን ቱፊታዊ አመጣጥ፣ አጠቃቀምና አንድምታዎች ከጊዜያቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲታወቁ እናም ጉድለትም ካለባቸው መሠረታቸውን ሳይለቁ ጥናትን መሠረት በማድረግ ክፍተታቸው እንዲሞላ አለማድረጋቸው ነው፡፡ ሌላው ይቅርና የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አይቀየርም፡፡ የሚያስተላልፈውም መልዕክት እንዲሁ፡፡

ነገር ግን እንደየትውልዱ አረዳድና የቋንቋ አጠቃቀም በሊቃውንት ጉባኤ በተወሰነ ጊዜ ይሻሻላል፡፡ ፊደሎቻችንና ቁጥሮቻችንስ እንዲሁ ቢሆኑ ምን ይል ነበር? በዚሁ የፊደሎቻችን ይሻሻሉ የምሁራን ጉባኤ ላይ ዛሬ በሕይወት የሌሉቱ ነፍሳቸውን ይማርና እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሠዓሊ አፈወርቅ ተክሌ ተጋባዥ ሆነው ቀርበው ስለነበር ጉባኤው የኃጢአት ምስክርነት እስከሚመስላቸው ሰቅጥጧቸው ተነስተው የተናገሩት እንደሚከተሉት እምነት የይሻሻሉ አቅራቢዎችን ‹‹ገዥቻችኋለሁ›› ነበር ያሉት፡፡ ለትውልዱም አደራ ያስተላለፉት ይኸንኑ የጥፋት መልዕክት እንዳይቀበል ነበር፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ሐሳባቸውን ያስተላለፉት ፊደሎቻችን ምንም እንከን የለባቸውም ብለው አቋም በመያዝ አልነበረም፡፡ ጉድለት ቢኖር እንኳን በጥልቀት እየተጠና መሠረቱን፣ ታሪካዊነቱንና ቅርስነቱን ሳይለቅ ወይም ሳይዛባ እንዲደፈን እንጂ፡፡

የሐበሻ ፊደሎቻችንና ቁጥሮቻችን ለዚህ ዘመን አጠቃቀምና ላለፉት ዘመናትም አስቀምጠውት እዚህ የደረሱበት ፋይዳና ያበረከቱት ድርሳናትን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማሻገር ያሉባቸው ችግሮች ሊጠኑ ይገባል፡፡ ያሉባቸው ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ አዎንታዊ ጐኖችም እንዲሁ፡፡ በመጀመርያ ሲፈጠሩ መሠረታቸው ምን ነበር? አሁን ላይስ እንዴት እየተገለገልንባቸው ነው? ወደፊትስ በምን ሁኔታ ለትውልድ እንዲተላለፉ ይደረጋል? የሚሉና ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥልቅ ጥናት ማድረጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሞክሼ ፊደላትም ሆኑ በአንድ ሥረ ግንድ ፊደል ከግእዙ እስከ ሳብዑ ባሉ ፊደላት መካከል ቅርፃቸው የተለያዩ ሆነው የሚሰጡት ድምፅ ግን ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የግእዝ ፊደላት ሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ አ፣ ዐ ከራብዑ ሥረ ግንድ ፈደላቸው ጋር ማለትም ሃ፣ ሓ፣ ኃ፣ ዓ ተመሳሳይነት ያላቸው ይመስላል፡፡ እንዲሁም በግእዝ ላይ ያሉት ከሣልስ ፊደላት ከራብዕ ፊደላት ወዘተ ጋር በድምፅ የሚመሳሰሉ የሚመስሉ አሉ፡፡ በእርግጥ ተመሳስለው ነው? የሚመሳሰሉም ስለሚመስሉን የተመቹንን ፊደላት በሥነ ጽሑፋችን እንጠቀምባቸዋለን ትክክል ነን? በምርጫስ መጠቀም ይኖርብናል?

ድምፃቸው ተመሳሳይ እየመሰለን ቅርፃቸውን እስከመርሳት የሚደርሱ ፊደላትም አሉ፡፡ ምሳሌ የ‘የ’ ሥረ ግንድ የሆነው ሣልሱ ‹‹ዪ›› እና ሳድሱ ‹‹ይ›› እንዲሁም ዲቃላ ፊደሎች፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ስንል ምናልባት በአነጋገር ዘይቤ (የአክሰንት)ለውጥ የፊደሎች ድምፅ ወደ ተመሳሳይነት ድምፅ ቀርበው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ምንን አስከተለ? ፊደላትን ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ከመሰለን በዘፈቀደ መጠቀምን፡፡ ለምን በዘፈቀደ መጠቀምን መረጥን? በመጀመርያ ብዙ አማራጭ በመኖሩ የመምረጥ ነፃነትን ከመፈለግ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በአጻጻፍ ከሌሎች ጋር በመቀራረባቸው ግርታ እንዳይፈጠር ለየት ያለውን ለመጠቀም ከመፈለግ፡፡ በተለይ ለጀማሪዎችና በእጅ ለሚጽፉ ጽሑፎች፡፡ ምሳሌ እሳቱ ‹‹ሰ›› ከ ‹‹ለ›› ጋር በምስልነት የተቀራረቡ ስለሚመስሉ እሳቱ ‹‹ሰ››ን ከመጠቀም ይልቅ ንጉሡ ‹‹ሠ››ን የመምረጥ አንፃር፡፡ በአራተኛ አውቀነውም ይሁን ሳናውቀው ከአስተሳሰባችን ጋር የተዋሐደውን የመምረጥ፡፡ እነዚህ ምርጫዎች ምን ችግር አመጡ? በጥልቀት መጠናት የሚገባው ይሆናል፡፡

የሰው ልጅ አመለካከቱን ቀድሞ የሚወስነው በአስተሳሰቡ የሚያሠርፀው ሥነ ልቦናዊ ምልከታውን ነው፡፡ ጐበዝ፣ ጐበዝ፣ ጐበዝ፣ . . . እየተባለ ያደገ ሕፃን በዋናነት ጐበዝ እንደሚሆንና ሰነፍ፣ ሰነፍ፣ ሰነፍ፣ . . . እየተባለ ያደገውም እንደዚሁ ስንፍናውን ተቀብሎ ተዋሕዶት የሚኖረው፡፡ የሁለቱም ተቃራኒ አስተሳሰቦች በሰዎች አስተሳሰብ ሲየርፁ የሚኖራቸው የሥነ ልቦና ተፅእኖ አላቸውና፡፡ እንደዚሁም አዎንታዊና አሉታዊ አስተሳሰብ የሚቆጣጠራቸው ሰዎች አሉ፡፡ ኦፕቲሚስትና ፔሲሚስት (Optimist and Pesmist) እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ አንዳንዶች በጎ ነገርን በመፈለግ ለማግኘት ይታክታሉ፡፡ በሒደት በጎ ያልሆነውን ቢገጥማቸው እንኳን በጎ አለመሆኑን ማጋነን ሳይሆን እንዴት በጎ ሊሆን እንደሚችል መፍትሔ ይሰጣሉ እንጂ፡፡ በሌላ ጽንፍ ደግሞ በጎ ያልሆነውን ችግር ችግሩን ለማግኘት ብቻና ይህንኑ አጉልቶ በማውጣት አጋኖ ለማጥላላት ሲባዝኑ ይታያሉ፡፡ እርካታውም ደስታውም በጎ ያልሆነውን ማግኘት ላይ ነውና፡፡ ይኸም አያስደንቅም የሰው ባሕሪ ነውና፡፡

መሬትና ከባቢ አየርም የተፈጠሩት ሁለቱንም ዓይነት ባህሪያትን ለመሸከም ነውና፡፡ በመሆኑም አንዱ ሌላውን ለመቀበል ወይም ለማጥፋት ማሰብ ግን የለብንም፡፡ ያም ሆነ ይህ ወደ ጀመርነው ርእስ እንመለስና የኛዎች የፊደል ጉድለት ‹‹ተቆርቋሪ ነን›› ባዮች ችግር ችግሩን ብቻ ለቅመው አጉልቶ በማሳየት የክተት አዋጅ እንዳያውጁ እነሱንም ጭምር በጥንታዊ ፈላስፎቻችንና በእነሱም ፈጣሪ ስም በጐውንም ያሳያቸው ለማለት እንጂ፡፡ በእርግጥ ‹‹ካልተበጠበጠ አይጠራም፣ በሽታውን ያልተናገረ መድኃኒት አያገኝም፣ ወዘተ›› የሚሉ መልዕክት አዘል ቱፊታዊ አባባሎች አሉን፡፡ ወደዚህኛው የፊደሎቻችን እንከን ላይ ስንመልሰው የፊደሎቻችንን ጉድለቶች ነቅሰው ማውጣታቸው ይበል፣ እሰየው፣ አበጃችሁ፣ ወዘተ ሊባሉ ይገባል፡፡ ይኸም በጉዳያዊ ጥናት (Case Studies) ሆኖ ለቀጣይ ጥልቅ ጥናቶች እንደ መነሻ መሆን ሲችል ነው፡፡ ነገር ግን ሮጦ ወደ ድምዳሜ መሔድ ግን ትዝብትም ብስጭትም ስለሚሆን ነው ጠንከር ያለ አስተያየት የተሰጠበት፡፡ አንዳንዴ እኛ ኢትዮጵያውያን የሚጐዳንን ችግራችንን በቅንነት ሲነገረንም እንደ ድፍረት የምንቆጥርና እምቧ ከረዩ የምንል ብዙ ነን እና፡፡ የሰላ ሒስ ወደ ጥልቅ ዕውቀት መውሰጃ ጎዳና መሆኑንም እንረዳው፡፡ ስለሆነም ይህ ጽሑፍ በዚህ አስተሳሰብ ተቃኝቶ የቀረበ እንጂ አዲስ ነገር ለማግኘት ምሁራዊ ትጋትን የሚከውኑ ወገኖቻችንን ለማስቀየም እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ምንጭ፤ሪፖረተር ጋዜጣ

-3-
የሀገር ውስጥ ምሁራን በፊደሎቻችን ላይ የሚያነሧቸው ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
በአምሳሉ አርጋው

የሀገር ውስጥ ምሁራን በፊደሎቻችን ላይ ብዙ ዓይነት ቅሬታዎችንና ጥያቄዎችን ሲያነሡ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በየብዙኃን መገናኛው ማለትም በየነጋሪተ ወጉ (Radio) በየምርአየኩነቱ (Television) እና በየ መጣጥፉ በማንሣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለውጦችንም ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም እንዲመቻቸው ይመስላል የፊደሎቻችን ባለቤት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ልቦናቸው እያወቀ እንደፈለጉ ያለከልካይ እና ጠያቂ ለውጥ ለማድረግ እንዲመቻቸው ከፊደላቱ ባለቤት ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተቃውሞ እንዳይነሣባቸው የፊደላቱን ባለቤት ለባዕድ ይሰጡታል ወይም የደቡብ ዓረቢያ ነው ብለው ይሰብካሉ፡፡ 100 ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ ጀምሮ ምሁራኑ በፊደሎቻችን ላይ ጥያቄ ሲያነሡ ቆይተዋል፡፡ የቀድሞዎቹ በተለየ ያነሡት የነበረ ጥያቄ እንደዛሬው መቀምር (Computer) ባልነበረበት ሰዓት የአማርኛ መጻፊያ መሣሪያ (typewriter) ለማሠራት የአማርኛ ፊደሎች በጣም ብዙ በመሆናቸው በሚል ሰበብ በእነሱ አባባል አላስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን በርካታ ፊደላት ማስወገድ ወይም መቀነስ ግዴታ ነው ብለው ይከራከሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የፊደላቱ መበርከት ታይፕራይተሩን ከመሠራት ሳያግደውና አማርኛን በታይፕራይተር መጻፍ እውን መሆን እንዳይችል ሳያደርገው ሁሉንም ፊደላት ባካተተ መልኩ ተሠርቶ በመምጣቱ በዚህ ምክንያት ተነሥቶ የነበረው የጦፈ ክርክር ለመዘጋት ቻለ፡፡

በጣም የሚያሳዝነውና እጅግ የሚገርመው ደግሞ ጥቂቶቹ ዚኖሜኒክ ምሁራን በገዛ ፊደሎቻችን መጠቀማችን ለዕድገት እንቅፋት ሆኖናል፡፡ መጠቀም ያለብን በላቲኑ ነው ይህን ብናደርግ ዕድገት እናመጣለን የሚሉ መገኘታቸው ነበር፡፡ በራሳችን ፊደላት መጠቀማችን እንዴት ሆኖ ለዕድገት እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ግን አሳማኝ አይደለም፡፡ እንዲያው የሚመስል እንኳን ማስረጃ አመክንዮ ወይም ሎጂክ ማቅረብ አልቻሉም ነበር፡፡ እግዚአብሔር መቼም በየዘመኑ ሰው አያሳጣምና በአንዳንድ ልበ ብርሃን ምሁራን በእነ አብዬ መንግሥቱ ለማ የማያዳግም ምላሽ ማለትም የራሷን ፊደል ጥላ በምዕራባውያኑ እየተጠቀመች ያለችውን ቱርክን የትም አለመድረስ የራሷን ፊደል መጠቀሟ ከዕድገት ያልተገታችውንና አስደናቂ ስኬት ያስመዘገበችውን ጃፓንንና የደረሰችበትን የስኬት ወይም የዕድገት ደረጃ በማንሣት በራስ ፊደላት መጠቀም ሊያግዝ ወይም ሊረዳ ቢችል እንጂ እንቅፋት ሊሆን እንደማይችልና መረጃም ሊቀርብበት እንዳልቻለ ወይም እንደሌለ በማሳየትና በመርታት ፊደሎቻችንን ሊታደጓቸው ችለዋል፡፡

ነገር ግን ሌሎች ያኔም ሲነሡ የነበሩ አሁንም እየተነሡ ያሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጥያቄዎቻቸውን ከመቶ ዓመታት ጀምሮ እስከ ዛሬ የሚያነሡትና በቂ መልስ ያልተሰጣቸውም አንዱና ዋነኛው ምክንያት መልስ ሊሰጡ የሚገባቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምሁራኑ ጥያቄዎችን የሚያነሡት ባልገባቸው ነገር ላይ በመሆኑ ጥያቄዎቻቸው የትም የማያደርሳቸው መሆናቸውን በማየት ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጧቸው ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሰዎች በየዩኒቨርሲቲው (መካነ ትምህርት) ከያዙት የወሳኝነት ሥልጣንና በፊደላቱ ዙሪያ ላሉ ነገሮች ሁሉ የሚመለከታቸው ወይም ተጠያቂዎች እነሱ እንደሆኑ ተደርጎ ከመታመኑ የተነሣ ያለ ዕውቀት ሳይገባቸው ትክክል መስሏቸው የሚወስኑት የተሳሳተ ውሳኔ ሥራ ላይ ሊውል የሚችልበት አጋጣሚና ሥጋት ወይም አደጋ በግልጽ እየታየ በመሆኑ ዝምታውንና ንቀቱን ወደ ጎን በመተው በቂና አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በማመን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ያገኘሁትንና የማውቀውን ያህል ተገቢውን ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡ በቀጥታ ወደ ጥያቄዎቹ ልሒድና ጥያቄዎቻቸው በራሳቸው አገላለጽ የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡

1. የፊደላቱ ብዛት ከሚገባው በላይ ተንዛዝቶና ገዝፎ እንዲታይ በመደረጉ በመማር ማስተማር ተግባር ላይ አላስፈላጊ ችግር ማለትም መሰላቸትን፣ መታከትን፣ መወሳሰብን፣ አስከትሏል፡፡ 2. ሞክሼ ፊደላት መኖራቸው በሥነ ጽሑፎቻችን ላይ የተዘበራረቀ የፊደላት አጠቃቀም እንዲከሰት አድርጓል፡፡ 3. የአናባቢ ወይም የድምፅ ሰጪ ምልክቶች ወጥ አለመሆን ወይም የተዘበራረቁ መሆናቸው እነእርሱን በቀላሉ ለማጥናት እንዳይቻል አድርጓል የሚሏቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ነገር ግን ምሁራኑ ያልተረዱት ነገር ቢኖር አባቶቻችን ያለበቂና አጥጋቢ ምክንያት ያደረጉት አንድም ነገር እንደሌለ ያለማወቃቸውን ነው፡፡ አሁን ጥያቄዎቻቸውን በተናጠል ከበቂ መልሶቻቸው ጋር እንይ፡-

ወደ መጀመርያው ጥያቄያቸው ወይም ቅሬታቸው ስናልፍ ማለትም የፊደላቱ ብዛት ከሚገባው በላይ ተንዛዝቶና ገዝፎ እንዲታይ በመደረጉ በመማር ማስተማር ተግባር ላይ አላስፈላጊ ችግር ማለትም መሰላቸት መታከት መወሳሰብ አስከትሏል ላሉት ችግር መፍትሔ አድርገው ያቀረቡት ነጥብ ሞክሼ ፊደላትን፣ ፍንድቅ ፊደላትን፣ የግእዝ ዲቃላ ፊደላትን በአጠቃላይ ከ91 በላይ ፊደላትን ማስወገድ ሲሆን አንዳንዶቹ ሻል ያሉቱ ደግሞ ፍንድቅ ፊደላትንና የግእዝ ዲቃላ ፊደላትን በምልክት መተካት ይላሉ፡፡ ይህን ጥያቄ ያነሡ ሰዎች ያልተረዷቸው ነገሮች ቢኖሩ፡-

ሀ/ ቋንቋችን አቡጊዳዊ (syllabary) ማለትም አናባቢንና ተነባቢን በአንድ ፊደል የወከለና ፎነቲክ ማለትም በቋንቋው ውስጥ ላሉ ድምፆች ሁሉ ለእያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ፊደል የሰጠ ወይም የቀረጸ ቋንቋ መሆኑን፡፡ በመሆኑም የፊደላቱ መበርከት ጨርሶ በጥያቄ መልክ ሊነሣ ባልተገባ ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ መሆኑ በዓለም ውስጥ ካሉ ቋንቋዎች እንዲደነቅ ያደረገውና ከማንኛውም ቋንቋ በተሻለ መልኩ ለብዙ ድምፆች ፊደል የቀረጸ በመባል በባዕዳን ምሁራን ሳይቀር ተደናቂ ያደረገው የቋንቋችን ባሕርይ መሆኑ ነው፡፡

ለ/ አሁንም ያልተረዱት ነገር ቢኖር ፊደላቱ በዝተዋል በሚል ከ24 በላይ ፍንጽቅ ፊደላትንና 20 የግእዝ ዲቃላ ፊደላትን ይወገዱ ሲሉ የሚያስወግዷቸው ፊደላቱን ብቻ ሳይሆን በፊደላቱ የተወከሉትን በንግግሮቻችን ውስጥ ያሉ ድምፆችን ጭምር ይወገዱ ማለታቸው እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ቢሆን ደግሞ የቋንቋውን ባሕርይና ምድቡንም ማለትም ከየትኛው የቋንቋ ዘር ውስጥ መሆኑን የሚገልጹትን ድምፆች እንዲያጣ ሊያደርገው መሆኑን፣ ቋንቋው ማለት የሚፈልገውን በቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ማለት እንዳይችል ወይም እንዳይገልጽ ሊሆን መሆኑን፣ በጽሕፈት ላይም ከእነዚያ ከተወገዱት ፍንጽቅ ፊደላትና የግእዝ ዲቃላ ፊደላት አንዷ የምትገልጸውን ድምፅ በመወገዳቸው ምክንያት ይወክሉት የነበረውን ድምፅ ለመግለጽ ከዚህ በኋላ እንደ አልፋቤቲካዊ ወይም ተናጠላዊ ቋንቋዎች በሁለት ፊደላት መግለጽ ግዴታ በመሆኑ በአንድ ገጽ የሚያልቅ የነበረው ጽሑፍ ከአንድ ገጽ በላይ እንዲገልጽ ሊያስገድደን እንደሆነ ነው፡፡ ይህም በደራሲው በሐዲስ ዓለማየሁ መጽሐፍ በፍቅር እስከ መቃብር ታይቷል፡፡ እራሳቸው ሐዲስ ዓለማየሁም ቢሆኑ የዚህ ዓላማ አራማጅ ሆነውም ጨርሶ ችግር አያመጣም አላሉም፡፡ የሚያስከትለው የንባብ ችግር ወይም የምሥጢር መፋለስና መሰወር ችግር ይህን ያህል አይደለም አሉ እንጂ፡፡ ነገር ግን ትንሽም ቢሆን በትክክሉ ማስቀመጥ ሲቻል አንዲትስ ብትሆን ለምን አግባብ ያልሆነ እንከን እናስቀምጥ?፡፡ አባቶቻችን ያንን ያህል እርቀው በንግግር ላሉ ድምፆች ሁሉ ፊደል በመቅረጽ ያለችግር ማለት የተፈለገን ነገር በትክክል እንዲባል እስከማድረግ ድረስ ርቀው በመሔድ ያደራጇቸውን ፊደላት በመቀነስ ቀደም ሲል ያየነውንና ቀጥሎ የምናያቸውን ችግሮች እንዲከሰቱ ማድረግ ማንም ሊረዳው እንደሚችለው የቋንቋውን ዕድገትና ብቃት ወደ ኋላ መመለስ ወይም ማንሸራተት እንጂ ዕድገት ወይም ችግር መቅረፍ ሊሆን አይችልም፡፡

አጥንቶ ለመያዝ ከአንድ ሰሞን በላይ የማይጠይቁትን ፊደላት ሲፈለጉ ብቻ ካልሆነ በስተቀር በፊደል ገበታቸው ቦታቸውን ይዘው አርፈው የተቀመጡትን ፊደላት አቀለልን በማለት ሲያስወግዷቸው ከዚያ በኋላ እነሱ ችግር ነው ከሚሉት በላይ መጽሐፍ ለመጻፍ ተጨማሪ ገጾችን መጠየቃቸው ይህም ደግሞ አንዳች ነገር ለመጻፍ በተፈለገ ጊዜ ሁሉ የግድ መሆኑ ከግለሰብ አልፎ በሀገር ጥሪት ወይም ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው አላስፈላጊ ወጪ ወይም ኪሣራ ጨርሶ አልታያቸውም፡፡ የዚህ ዓላማ አራማጅ የነበሩት ሐዲስ ዓለማየሁ መጽሐፋቸውን እንደዚህ አድርገው ይጻፉት እንጂ በንግግራቸው ግን ጨርሶ ሊተገብሩት አልቻሉም ነበር፡፡ ሊተገብሩትም አይችሉም፤ ምክንያቱም ቋንቋችን ፎነቲክ ነውና ማለትም ለእያንዳንዱ ድምፅ የየራሱን ፊደል የቀረጸና እንደ ፎነቲክነቱም ለእያንዳንዱ ድምፅ ፊደል የመቅረጽ ግዴታ ስላለበት፡፡ ቋንቋችን ፎነቲክ የሆንው በምርጫ ወይም ተፈልጎ አይደለም፤ ነገር ግን ተፈጥሯዊ ባሕርይው ስለሆነ እንጂ፡፡ ቋንቋችን በተፈጥሮው አቡጊዳዊ ወይም ሲለበሪ መሆኑ ነው ፊደሎቻችን አቡጊዳዊ ወይም ሲለበሪ ማለትም አናባቢና ተነባቢን በአንድ ፊደል የሚወክሉ እንዲሆኑ የተገደዱት፡፡ ፊደሎቻችን ሳይፈጠሩ በፊትም የቋንቋችን ድምፆች በተፈጥሯቸው ስንናገራቸው አናባቢና ተነባቢ በአንድ ላይ ተቀላቅለው ወይም ተደምረው ነው የሚወጡት፡፡ ለምሳሌ በድምፅ ውስጥ እራሱ ‹‹ብ›› እና ‹‹ኧ›› ድምፆች ተቀላቅለው ነው የሚወጡት፣ ቡ ስንል ደግሞ ‹‹ብ›› እና ‹‹ኡ፣ ቢ ስንል ደግሞ ‹‹ብ›› እና ‹‹ኢ›› በዚሁ መልኩ ሁሉንም ሆሔዎች ስንጠራ በውስጣቸው የአናባቢ ድምፆች አብረው ይኖራሉ፡፡ ይሄም በመሆኑ ነው ፊደል ሲቀረጽላቸውም አናባቢንና ተነባቢን በአንድነት የሚገልጹ ሆነው የተገኙት፡፡ ይሔ እንግዲህ ምንም ልናደርገው የማንችለው ተፈጥሯዊ ባሕርይው ነው፡፡

ይህንን ከላይ የገለጽኩትን የቋንቋችንን ተፈጥሯዊ ባሕርይ የሚያውቅና የተረዳ ሰው በምንም ተአምር ቋንቋችን ለእያንዳንዱ ድምፅ ፊደል መቅረጹን ሊቃወም ወይም ላይቀበል አይችልም፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ቋንቋችን ለብዙ ድምፆች ለየራሳቸው ፊደል በመቅረጹ የሚያክለው ወይም የሚስተካከለው ቋንቋ ባለመኖሩ እጅግ ተደናቂ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ምሁራኑ ይህንን ጥያቄ ሲያነሡ እኔ የሚገባኝ ምንድ ነው? ሰዎቹ ምን ያህል የገዛ ቋንቋቸውን ባሕሪ በጥልቀት ያለመረዳታቸውንና ባልተረዱት ነገር ላይ ለውሳኔ መቸኮላቸውን ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ሰዎች በቋንቋ ጥናት የዶክትሬትና የፕሮፌሰርነት ማዕርግ ከዚያም በላይ ያላቸው መሆናቸው ነው፡፡

ሐ/ የቋንቋው የድምፅ ሥርዓት የሚበላሽ መሆኑን ማለትም አዳዲስና ከአማርኛ ቋንቋ የልሳን ድምፆች ውጭ የሆኑ ወይም ያልነበሩ የተንሻፈፈና የተወላገደ የአፍ አከፋፈት፣ የምላስ መተሣሠር የሚያስከትሉ አዳዲስ ድምፆች የሚከሠቱ መሆናቸውን፡፡ ለምሳሌ ባሏ ለማለት ባልዋ፣ ሲሟሟ ለማለት ሲሙዋሙዋ፣ ሲሯሯጡ ለማለት ሲሩዋሩዋጡ፣ እሷ ለማለት እሱዋ፣ ሿሚ ለማለት ሹዋሚ፣ ቋንቋ ለማለት ቁዋንቁዋ፣ ቧልት ለማለት ቡዋልት፣ ፊቷ ለማለት ፊቱዋ፣ ወንድሞቿ ለማለት ወንድሞቹዋ፣ ኋላ ለማለት ሁዋላ፣ ኗሪ ለማለት ኑዋሪ፣ እንኳን ለማለት እንኩዋን፣ ዟሪ ለማለት ዙዋሪ፣ አንዷ ለማለት አንዱዋ፣ እጇ ለማለት እጁዋ፣ ጓደኛ ለማለት ጉዋደኛ፣ ጧሪ ለማለት ጡዋሪ፣ ጯሂ ለማለት ጩዋሂ፣ ፏፏቴ ለማለት ፉዋፉዋቴ ወዘተ እየተባሉ ሲጻፉ ሲነገሩ ሲነበቡ ማንም እንደሚገነዘበው ለአንደበት ካለመመቸታቸውም ባሻገር ለጆሮ የሚሰጡት የድምፅ ቃና ጥሩ ባለመሆኑ የቋንቋችንን የጥራት ደረጃ የሚያወርድ የሚያጎል እንጂ እሴት የሚጨምር አለመሆኑን፡፡

መ/ ሞክሼ ፊደላት ቢወገዱ የሚከሰቱትን የምሥጢርና የትርጉም መፋለስን፡፡ ሞክሼ ፊደላትንም አባቶቻችን ያለጥቅምና ያለበቂ ምክንያት እንዳልፈጠሯቸው መረዳት አልተቻላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሞክሼ ፊደላት አጠቃቀም የራሳቸው የሆነ ዶግማዊ አይዶሎጂያዊ ወይም ርእዮተ ዓለማዊ እና መለያዊ ምክንያቶች ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን ሦስት ምክንያቶች በምሳሌ እንይ፡- በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አምስት አዕማደ ምሥጢራት አሉ፡፡ ከእነዚህ ሦስቱ በፊደላት አጠቃቀም የታሠሩ ናቸው፡፡ እነዚህም ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ እና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው፡፡ ወደ ምሥጢረ ሥላሴ ስንሔድ ሦስቱ ቁጥር በፊደል ሲጻፍ በንጉሡ ሠ ወይም በሠራዊቱ ሠ ሳብዑ ነው፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃልም ሲጻፍ በንጉሡ ሥ ነው፡፡

ሥላሴና ሦስት በአንድ የሠ ቤት መጻፋቸው ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው የሚለውን ዶግማዊ አስተምህሮ እንዲገልጽና እንዲይዝ በማሰብ ነው፡፡ ከዚህ ወጥቶ ግን በእሳቱ ሳ ቢጻፍ የሚገልጹት ቃል ወይም ትርጉም ሌላ ይሆናል፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌ ሲጻፍም በንጉሡ ወይም በሠራዊቱ ሠ ሳድሱ ነው፡፡ ሥጋ ሲጻፍም በዚያው ሥ ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ሥጋ በተጻፈበት ሥጋዌ መጻፉ ‹‹መለኮት ሰው ሆነ ሥጋ ለበሰ›› የሚለውን ዶግማዊ ምሥጢር እንዲይዝ ታስቦ ነው፡፡ ትንሣኤ ሲጻፍ የሚጻፈው በንጉሡ ሥ ራብዑ ነው፡፡ ትንሣኤ ማለት መነሣት ማለት ነው፡፡ በዚሁ ‹‹ሣ›› መጻፉ ቀርቶ በእሳቱ ‹‹ሳ›› ቢጻፍ መነሣት የሚለው ትርጉም ይቀርና አከላከል ወይም መከልከል የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ይህም በመሆኑ ምሥጢር ይፋለሳል፣ መባል የተፈለገው ሳይባል መባል ያልተፈለገው ይባላል ማለት ነው፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ ፊደላቱ ቢለዋወጡ ችግር የሚያመጡ ኅቡአት የእግዚአብሔር ስሞች ብዙ አሉ፡፡ ከዶግማዊ ምክንያቶች እነዚህን ካነሣን ይበቃል፡፡ ወደ አይዶሎጂያዊ ወይም ርእዮተ ዓለማዊ ምክንያቶች ስንሔድ ደግሞ ክቧ ዐ ዐይኗ ዐ በመባል ትታወቃለች፤ ዐይን ሲጻፍም የሚጻፈው በዚህችው ዐ ነው፡፡ ዐይኗ ዐ የተባለችበት ምክንያትም የዐይን ቅርጽ በመያዟ ወይም ዐይን በመምሰሏ ምክንያት ነው፡፡

ወደመለያዊ ምክንያት ስንሔድ ደግሞ በአል የሚለው ቃል በአልፋው አ ሲጻፍ አይሁድ ያመልኩት የነበረን ጣዖት ስም ያመለክታል፡፡ በዓይኑ ዐ ራብዑ ሲጻፍ ደግሞ ልዩ ቀን የተከበረ ቀን የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ዓመት የሚለው ቃል በዐይኑ ዐ ራብዑ ሲጻፍ 12 ወራት ከ5 ወይም ከ6 ቀናት ማለት ሲሆን፣ ዓመት የሚለው ቃል በአልፋው አ ሲጻፍ ደግሞ አገልጋይ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ‹‹አኅያ›› ማለት የእግዚአብሔር ኅቡእ ስሙ ነው፡፡ ሲነበብም ላልቶ ነው የሚነበበው ‹‹አህያ›› ደግሞ ከእንስሳት አንዱ የበቅሎ አባት ወይም የፈረስ አጎት ማለት ነው፡፡

ሠዓሊ የሚለው ቃል በንጉሡ ሠ እና በዓይኑ ዐ ራብዑ ሲጻፍ ሥዕል የመሣል ሙያ ያለው ማለት ሲሆን፣ ሰአሊ የሚለው ቃል በእሳቱ ሰ እና በአልፋው አ ሲጻፍ ደግሞ ለማኝ፣ ተማጻኝ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ አራት በአልፋው አ ሲጻፍ ከሦስት ቀጥሎ የሚገኝን ቁጥር ሲያመለክት በዐይኑ ዐ ሲጻፍ ደግሞ መኝታ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ሠረቀ የሚለው ቃል በንጉሡ ሠ ሲጻፍ ወጣ፣ ታየ፣ ተገለጠ፣ ብቅ አለ፣ በራ የሚል ትርጉም ሲኖረው በእሳቱ ሰ ሲጻፍ ደግሞ ለበየ፣ ወሰደ፣ አጠፋ፣ ደበቀ፣ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ ምሁር የሚለው ቃል በሀሌታው ሀ ሲጻፍ የተማረ ያወቀ የመጠቀ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ በሐመሩ ሐ ካዕቡ ሲጻፍ ደግሞ ምሕረት ያገኘ የሚል ትርጉም ይይዛል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ብዙ ቃላት አሉ፡፡ እንግዲህ በግልጽ እንደሚታየው አባቶቻችን ይህን ያደረጉበት ወይም ሞክሼ ፊደላትን የፈጠሩበት ምክንያት የቃላት መመሳሰል ሲያጋጥም በፈደላቱ በመለያየት የየራሳቸውን ትርጉም እንዲይዙና አሻሚ እንዳይሆኑ ለማድረግ ነው፡፡ የሞክሼ ፊደላት አገልግሎት ይሄ ነው እንጂ ቀድሞ የተለየ ድምፅ ኖሯቸው ያድምፃቸው አሁን ጠፍቶ ወይም ተረስቶ አይደለም፣ ይህ አስተሳሰብ የተለየ ድምፅ ከነበራቸው አሁን ላይ ያ ድምፃቸው ጠፍቷልና ወይም ተረስቷልና ፊደላቱ ጥቅም የላቸውም ማለት ነው፤ ስለዚህም ይወገዱ ለማለት የተፈጠረ ሰበብ ነው፡፡ እውነቱና የፊደላቱ አገልግሎት ግን ከላይ በምሣሌዎች እንዳየናቸው ነው፡፡

ምሁራኑ ግን ፊደላቱ ያላቸውን አገልግሎትና ቢጐሉ የሚያስከትሉትን ችግር ባለማጤን ወይም ባለማወቅ እንደ ትርፍና አላስፈላጊ ቆጥረዋቸዋል፡፡ እነኚህ ምሁራን በእንደነዚህ ዓይነት ማብራሪያዎች ወገባቸው ሲያዝ አሁን አሁን ደግሞ ምን ማለት ጀምረዋል? እሺ ለግእዝስ ይሁን ሞክሼ ፊደላት ለአማርኛ ግን አይጠቅሙምና ከአማርኛ ይወገዱ ማለት ጀምረዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን አንድ ያልተረዱት ጉዳይ አለ፡፡ እሱም አማርኛ ቋንቋ በራሱ የቆመ ቋንቋ አለመሆኑን ወይም ያለግዕዝ ድጋፍ ቋንቋ ሆኖ ማገልገል የማይችል መሆኑን፣ ከግሶቹ እና ቃላቱ የሚበዙቱ ግእዝ መሆናቸውን አለማወቅ፣ ከግእዝ ፈጽሞ መነጠል የማይችል ወይም እራሱን የቻለ ቋንቋ አለመሆኑን ያለመረዳታቸውና በዚህ ምክንያትም የሞክሼ ፊደላቱን አገልግሎት የግዱን የሚጋራ መሆኑን ካለማወቅ የተነሣ ይህንን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በአጠቃላይ ችግር ነው ብለው የሚገልጹትና መፍትሔ ነው ብለው የሚያቀርቡት አራምባና ቆቦ እንደሚባለው የማይገናኙ ብቻ ሳይሆኑ በተቃራኒው አቅጣጫ ሲነጉዱ ይታያል፡፡

ከእነዚህኞቹ የተሻሉ ናቸው የተባሉት ፍንጽቅ ፊደላትንና የግእዝ ዲቃላ ፊደላትን ከማስወገድ ይልቅ በምልክት መተካት የሚሉቱ ለእንዲህ አይነት ውሳኔ የዳረጋቸው ምክንያትና ድርጊታቸው ወይም ውሳኔያቸው ፈጽሞ የሚጣጣም አይደለም፤ እነሱ እንዲህ እንዲሆን የፈለጉበትን ምክንያት ሲገልጹ ፊደሎቹ በጣም ከመብዛታቸው የተነሣ ለጀማሪ ፊደል ቆጣሪ የተወሳሰበ አድርጎታል ብለው ሲያበቁ ለመፍትሔአቸውም ሲሉ የፊደላቱን ቁጥር መቀነስ ላይ ብቻ ሲያተኩሩ መወሳሰብን ለማስወገድ ያሉትን የመፍትሔ መንሥኤያቸውን እረስተውት ከአርባ በላይ ፊደላትን በወረቀት ላይ ግዘፈ አካል ነስተው የሚታዩና የሚታወቁ የነበሩትን ፊደላትን በአንዲት ምልክት ተክተው የማይታዩ አደረጓቸው፣ ይሄም መሆኑ ጭራሽ እንኳን ለጀማሪ ፊደል ቆጣሪ ይቅርና ፊደል ለለየውም እንኳን ከአርባ በላይ የተለያዩ ድምፆችና የተለያዩ የድምፅ ቅላጼ ወይም ፎኒም ያላቸውን ፊደላት አንድ ምልክትን ከሀ ለ ሐ መ ው ካሉት አምሳያ ፊደሎቻቸው ጋር በማቀናጀትና በመጠቀም ከአርባ በላይ የፍንጽቅ ፊደላትንና የግእዝ ዲቃላ ፊደላትን እንዲፈጥሩ ማድረግ በጣም የተወሳሰበና ከባድ አደናገሪም እንዲሆን ማድረጋቸው ጨርሶ ሳይታወቃቸው ቀርቶል፡፡ ልብ በሉ ይህንን ያደረጉት ግን መወሳሰብን ለማስወገድ በሚል ነው፡፡

ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ችግር ነው ብለው የሚያወሩትና መፍትሔ ነው ብለው የሚያቀርቡት ሐሳብ ጨርሶ ባለመጣጣሙ እነዚህ ሰዎች ደኅና የነበረውን መፍትሔ ነው እያሉ ጭራሽ የተወሳሰበ ችግር የሚፈጥሩበት እንዲህ የሚያደርጋቸው ፊደላቱን የሚያስጠላቸው ዐይነ ጥላ ይሆን ያሰኛል፡፡ ወደ ሁለተኛው የፊደል ገበታችን አለበት ወደ አሉት ችግር ስናልፍ፡-

በሥነ ጽሑፎቻችን ላይ የተዘበራረቀ የፊደላት አጠቃቀም መከሰቱ ላሉት ችግር መፍትሔ ነው ብለው ያቀረቡት ሐሳብ አሁንም ሞክሸ ፊደላትን ማስወገድ የሚል ነው፡፡ በእውነቱ ከሆነ ይሄ የመፍትሔ ሐሳብ ከአንድ ያልተማረ ሰው ቢሰነዘር ኖሮ አይደንቀኝም ነበር፤ ነገር ግን ምሁራን ከተባሉና የችግሮች መፍትሔ መማር ወይም ማወቅ የሕይወት መርሐችን ነው ከሚሉ ሰዎች ግን ይሄ መሰንዘሩ እጅግ የሚያሳዝንና እነርሱንም ለትዝብት የሚዳርግ ነው፡፡ እንደ ምሁር መፍትሔ ሊያደርጉት የሚገባው እስከ አሁንም ድረስ አዋቂዎች ሲያደርጉት እንደቆዩት ሁሉ የፊደላቱን አጠቃቀም በማጥናት እንደሚገለገሉበት ሁሉ መፍትሔው አጠቃቀማቸውን ማጥናት ነው ብለው ይላሉ ብዬ እጠብቅ ነበር፤ በቀላሉ በዚህ መንገድ ችግሩን መፍታት ሲቻል የፊደላቱን አጠቃቀም እንደ ርእሰ ኃይል መጣቅ (Nuclear Science) አክብደው በማየት መፍትሔው መሆን ያለበት ፊደላቱን ማስወገድ አድርገውት ዐረፉ፡፡ ሌላው ቢቀር ፊደላቱ ቅርሶችም ናቸውና ስለ ቅርስነታቸው ብለው እንኳን ሊሳሱላቸው አልቻሉም፡፡ በጣም የሚገርመው እንዲህ ሞክሸ ፊደላት የሚለይላቸው ቃላት በዙሪያችን ከምናውቃቸው ሰዎች ስሞች የማይበዙ ወይም የማይበልጡ መሆናቸው ነው፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነኝህን ፊደላት የሚለይባቸውን ቃላት ከሚለይባቸው ምክንያት ጋር ሰብስበው በመጽሔት ቢገልጿቸው ይህ ጥያቄ እንዳይነሣ ከማድረግ አኳያ ጥቅሙ ከፍተኛ ነውና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲያስቡበት ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

ወደ ሦስተኛው የፊደል ገበታችን አለበት ወዳሉት ችግር ስናልፍ የአናባቢ ወይም የድምፅ ሰጪ ምልክቶች ወጥ አለመሆን ወይም የተዘበራረቁ መሆን ለማጥናት አስቸጋሪ ስላደረገው ወጥና ተመሳሳይ ድምፅ ሰጪ ምልክቶች ለካዕቡ አንድ ዓይነት ለሣልሱ እስከ ሳብዑ ድረስ ለየቤታቸው አንድ አንድ ዓይነት የድምፅ ሰጪ ምልክቶች መኖር አለበት የሚል ውሳኔ ላይ ደርሰው በፊደሎቻችን ላይም እንዳሉት የቅርጽ ለውጥ አድርገውባቸው ለማሳየት ሞከሩ፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ የተቀየረው የፊደል ገበታ ጭራሹን በችግር የተሞላ ሆኖ ይታያል፡፡ አባቶቻችን ምሁራኑ እንዳሉት ለየፊደላት ቤቶች ወጥና አንድ ዓይነት የድምፅ ሰጪ ምልክት እንዳያደርጉ ያደረጋቸውና ፊደላቱን አሁን ባሉበት ሁኔታ የቀረጹበት ምክንያቶች ወይም መለኪያዎች መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ. ፊደላቱን ለመጻፍ ከሚጠይቁት የቦታና የጊዜ ፍጆታ ቁጠባ አንፃር ለምሳሌ ላ፣ ሓ፣ሳ፣ሻ፣ባ፣ኣ፣ካ፣ኻ፣ዛ፣ዣ፣ጣ፣ጳ፣ጻ ወዘተ እንደእነ ቃ፣ታ፣ቻ፣ያ፣ጋ፣እና ፓ ግራ እግራቸውን ወይም ቀኝ እግራቸውን ወደ ግራ በማጠፍ የራብዕ ድምፅ ቤት እንዲፈጥሩ ያላደረጉበት ምክንያት አሁን ካሉበት ሌላ ተጨማሪ የቦታ ፍጆታ እንዲወስዱ ስለሚያደርጋቸውና ያ ደግሞ እነሱን ለመጻፍ ተጨማሪ የጊዜ ፍጆታ እንዲጠይቁ ስለሚያደርጋቸውና ይህ እንዲሆን ደግሞ ስላልተፈለገ ነው፡፡

ለ. ውበታቸውን ከመጠበቅ አንፃር ለምሳሌ ከላይ በእነ ላ፣ ሓ፣ሳ፣…ተርታ የተጠቀሱት ፊደላት ከእነሱ በታች እንደተጠቀሱት ማለትም እንደነ ቃ፣ታ፣ቻ፣…የግራ ወይም የቀኝ እግራቸውን ወደ ግራ በማጠፍ የራብዕ ድምፅ እንዲፈጥሩ ያላደረጉበት ምክንያት አሁን ካሉበት የሚያምር ቅልብጭ፣ ቅልጥፍ፣ ቅልል ያለው አካላቸው ተበላሽቶ ኮተታም የሚያደርጋቸውና ውበታቸውን የሚያበላሽ ሆኖ ስላገኙት ነው፡፡

ሐ. የእራሳችንን ብዙ አማራጮች የመፍጠር ክህሎትን ወይም ችሎታን ከማሳየትና የዚህም ባለቤቶች መሆናችንን ከማሳየት አንፃር፣

መ. ፊደሎቻችን ያላቸውን አካለ ሰለጣዊ ወይም ጅምናስቲካዊ የመተጣጠፍ ተፈጥሯአዊ ክህሎት ወይም ችሎታቸውን ከማሳየት አንፃር፣

ሠ. መመሳሰልን ከማስወገድ አንፃር ለምሳሌ የኮ፣ ጎ፣ ቆ እና ኆ ከጐናቸው እዝል ወይም ቀለበት በማድረግ የሳብዕ ድምፅ እንዲፈጥሩ ያልተደረገበት ምክንያት ከግእዝ ዲቃላ ፊደላት ከሚባሉት ፊደላት ጋር የሚመሳሰሉ ሆነው በመገኘታቸው ምክንያት የተለየ የሳብዕ ድምፅ የሚፈጥር ምልክት እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡

እናም አባቶቻችን እነዚህን አምስት መለኪያዎች እያዩና እየለኩ እየመዘኑ ፊደላቱን በምናውቃቸው መልኩ ሊቀርጿቸው ችለዋል፡፡ ምሁራኑ ግን እነኚህን ቁምነገሮች ሳያውቁ ትዝብት ላይ ሊጥላቸው ከሚችል ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ቻሉ፡፡ በአማራጭነት ያቀረቧቸው የተለያዩ የፊደል ገበታዎችም ካሏቸው ችግሮች የተነሣ ዓይን የሚስቡ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ ለውጥ የተደረገበትን የፊደላቱን የራብዑን ቤት ስናይ ሁሉም ፊደሎች ልክ እንደ ቀ፣ ተ፣ ቸ፣ የ፣ ገ እና ፐ ቤቶች እግሮቻቸውን ወደግራ በማጠፍ የራብዕ ድምፅ መፍጠር አለባቸው ብለው በመነሣታቸው ፊደሎቹ በነባሩ የፊደል ገበታ ሲጻፉ ይወስዱ ከነበረበት ቦታ እንደገና ሌላ ተጨማሪ የቦታ ፍጆታ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ደግሞ በፊት እነሱን ለመጻፍ ይጠይቁ ከነበረው የጊዜ ፍጆታ ተጨማሪ የጊዜ ፍጆታ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል፡፡

ከውበት አንፃር ሲታዩም ደግሞ ከነበራቸው አካልና መልክ ተጨማሪ ጭረት እንዲሸከሙ በመደረጋቸው ጭረት የበዛባቸውና ቡቱቷም፣ ተመሳሳይ ከመሆናቸው አንፃርም አሰልቺ አድርጓቸዋል፡፡ አባቶቻችን ያሳዩትን ብዙ አማራጭ የመፍጠር ችሎታንም ጠርጐ በማስወገድ ፊደሎቹ በሙሉ በየቤታቸው ተመሳሳይ በመሆናቸው ፊደላቱ በነባሩ የፊደል ገበታ ላይ የነበራቸውን አጫዋችነትንና አመራማሪነትን እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ የተለያዩ አካለ ሰለጣዊ ወይም ጅምናስቲካዊ የመተጣጠፍ ችሎታቸውንም አስወግዶ አቅመ ደካማ ውሱንና የተቀየዱ አድርጓቸዋል፡፡ በነዚህም ምክንያቶች እንኳን ለመገልገል ለማየትም ትዕግሥትን የሚፈታተን የፊደል ገበታ ሊሆንባቸው ችሏል፡፡ በተለይም ደግሞ አንድ የሳቱት ትልቅ ቁምነገር ቢኖር እነኚህ እነሱ አሻሻልን ካሏቸው ሁለት ሦስት የፊደል ገበታዎች አንዱ በአገልግሎት ላይ ቢውል ከዚህ በፊት በነባሮቹ ፊደሎቻችን በተጻፉት የሀገራችን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶቻችንና መጻሕፍት ላይ ሞት መፍረድ ወይም ተደራሽ ተነባቢ እንዳይሆኑ ማድረጋቸው እንደሆነ የተረዱት አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ቀጣዩ ትውልድ እነዚህ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶቻችን የተጻፉበትን ፊደል የማያውቅ ይሆናልና፡፡ በአጠቃላይ ቋንቋችን ሲላቢካዊ ወይም አቡጊዳዊ መሆኑ እንደላቲኑ አልፋቤቲካዊ ወይም ተናጠላዊ አለመሆኑ ከብዙ ዓይነት ጣጣዎች እንዲድን አድርጐታል፡፡

ለምሳሌም እንግሊዝኛ ቋንቋ አልፋቤቲካዊ ወይም ተናጠላዊ በመሆኑ እንደእኛ ሲላቢካዊ ወይም አቡጊዳዊ ባለመሆኑ ማለትም አናባቢንና ተነባቢን በተከታታይ በመደርደር የሚጻፍ በመሆኑ ለአላስፈላጊ የገንዘብና የጊዜ ብክነትና ኪሣራ እንዲዳረጉ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ ይህንኑ ‹‹Alphabetical›› የሚለውን ቃል በላቲን ፊደላት ሲጻፍ 12 ፊደላትን ማስፈር ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን የላቲኑን ትተው ማለትም አንዲትን ድምፅ ለመግለጽ ከሁለት እስከ አራት ፊደላትን መደርደር የሚገደደውን አጻጻፍ ትተው በእኛው ሲላቢካዊ ወይም አቡጊዳዊ በሆነው ማለትም አናባቢንና ተነባቢን በአንዲት ፊደል ብቻ በሚገልጸው ፊደላችን ቢጽፉት ሰባት ፊደላት ብቻ በማስፈር ማለት የፈለጉትን ቃል መግለጽ በቻሉ ነበር፡፡ ብዙዎች ቃላቶቻቸው በነሱ አጻጻፍ ሲጻፉ የሚወስዷቸው የፊደላት ብዛት በኛ ሲጽፉት ከግማሽ በታች የፊደላት ብዛት መግለጽ የሚቻሉ ናቸው ፡፡ ሌላም አንዲት አጭር ቃል ብናይ ‹‹thickness›› የሚለው ቃል በላቲኑ ሲጻፍ ዘጠኝ ፊደላትን ማስፈር ግዴታ ነው፡፡ በእኛ ፊደላት ሲጻፍ ግን አራት ፊደላትን ብቻ በማስፈር የአምስቱን ፊደላት ቦታ በማትረፍ ማለት የተፈለገውን ቃል ማስፈርና መቆጠብ በቻሉ ነበር፡፡ ይህም ማለት ከግማሽ በላይ የሆነ ኪሳራን ማስወገድ ወይም ፍጆታን ማዳን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ገምቱት ከዚህች አንዲት ቃል ብቻ የአምስት ፊደላትን ቦታ ማትረፍ ከተቻለ ከመጽሐፍ ሲሆን ደግሞ አስቡት ከግማሽ ላላነሰ ለገንዘብ፣ ለጊዜና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ብክነት ተዳርገዋል ማለት ነው፡፡

በ50 ገጽ ማለቅ የሚችለው መጽሐፍ በ100 እና ከዚያም በላይ ገጾች እንዲያልቅ ይገደዳሉ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም በላቲኑ የአጻጻፍ ዘዴ አንድ ፊደል ሁለትና ከዚያ በላይ የተለያዩ ድምፆችን እንዲወክል በመደረጉ የቋንቋውን ባለቤቶች ሳይቀር አገልግሎት ላይ ሲቸገሩ በየፊልማቸው (በየምስናዳቸው) ከአስቂኝ ሁኔታዎች ጋር ሲቸገሩ የሚገልጹትና የምናስተውለው ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹G›› ፊደል ከአናባቢዎች ጋር በመሆን እንደ ጀ፣ ጃ፣ ገ፣ ጉ፣ ጊ፣ ጋ፣ ግ፣ ጎ እንዲነበብ መደረጉ፡፡ ‹‹C›› ፊደል ከአናባቢዎች ጋር በመሆን እንደ ሰ፣ ሳ፣ ሴ፣ ከ፣ ኩ፣ ካ፣ ክ እና ኮ እንድትነበብ፡፡ ‹‹U›› ደግሞ እንደ አ፣ ኡ፣ ዩ እንድትነበብ በመደረጉ ሌሎችም እንደዚያው፡፡ በተጨማሪም ተጽፈው ሲያበቁ የማይነበቡ ወይም ሳይለንት ፊደላት መኖር ይሄንን እንዲደርጉ ያስገደዳቸው ደግሞ እንደኛ ሞክሼ ፊደላት ስለሌሏቸውና የቃላት መመሳሰል ሲፈጠር ለመለያየት ከፊቱ ወይም ከመሀሉ ሌላ ባዕድ ፊደል ይደነቅሩበታል፡፡ ለምሳሌ ‹‹rite›› እና ‹‹write›› ሲነበቡ ሁለቱም ራይት ተብለው ነው የሚነበቡት ሲጻፉ ግን የግድ አንዱን ከሌላው ለመለየት ከድምፁ ወጪ ባዕድ ቃል እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም አንዳች ነገር ለመጻፍ በፈለጉ ጊዜ እራሳቸው ተወላጆቹ መዝገበ ቃላትን ጨብጠው ካልሆኑ በስተቀር የማይሆን መሆኑ፡፡

እንግዲህ ከእነዚህና ከሌሎችም ጣጣዎች ሁሉ የእኛ ቋንቋ የተረፈው ወይም የዳነው ቋንቋችን ፎነቲክ እንዲሆን ወይም ለእያንዳንዷ ድምፅ የየራሱ ፊደል እንዲኖረው በመደረጉና አቡጊዳዊ ወይም ሲላቢካዊ በመሆኑ ነውና የፊደላቱ መበርከት ለጥቅምና በአጥጋቢ ምክንያት የተደገፈ በመሆኑ ምሁራኑ እንደሚሉት ለማታከት እንዳልሆነ ተረድተው ይህንን ያደረገልንን አምላክና ምክንያት የሆኑትን አባቶቻችንን ማመስገን ይኖርባቸዋል ብዬ እመክራለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እግዚአብሔር ይመስገንና የአባቶቻችንን ድካም በሚገባ የተረዱ ብዙ ምሁራንም አሉን፡፡ ቅሬታ ያለባቸው ምሁራንም ቢሆኑ ሁሉም ያነሧቸው ነጥቦች ውድቆች ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ትክክለኛ የሆኑ ቅሬታም እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ በጽሑፍ ላይ የሚጠብቀውና የሚላላውን የሚለዩ ምልክቶች ስለሌሉ ብዙ ቃላት በአነባበብ ሒደት ላይ አሻሚ ሲሆኑ እንደ አውዳቸው (Contextually) እንድናያቸው ሲያደርጉን ይታያሉ በሚል ያነሡት ቅሬታ ትክክል ነው፡፡ ከሌላ ቦታ ሌላ ምልክት ማምጣት ወይም መፍጠር ሳያስፈልገንም ቅዱስ ያሬድ ለዜማ ምልክትነት የፈጠራቸውን ምልክቶችን በመጠቀም ይህንን ችግር መቅረፍ ይቻላል፣ ይኖርብናልም፡፡

ዓለም የቅዱስ ያሬድን የዜማ ምልክቶች ሌላው ዓለም እንዴት ለየቋንቋው በሥርዓተ ነጥብነትና በድምፅ ምልክትነት እንደተጠመቀበት ዕድሜ ለኪነ ብጀታ (Technology) የተለያዩ ድረ ገጾችን ስናይ ምን ያህል እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡

ምንጭ፤ሪፖረተር ጋዜጣ

-4- 

የፊደል ጣጣና የአምስቱ ትውልድ ውዝግብ! 
በሰሎሞን ተሰማ ጂ. 

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” (1948) በታተመው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደበየኑት፣ “ፊደል ማለት ቀለም፤ ምልክት፤ የድምፅና የቃል መልክ፤ ሥዕል፤ መግለጫ ማስታወቂያ፤” ነው (ገጽ 616)። ደስታ ተክለ ወልድም በበኩላቸው፣ በ1962 ዓ.ም. ባሳተሙት “ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት” መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ “ፊደል ማለት የነገር፣ የቃል ምልክት፣ የድምፅ ሥዕል፣ ማጉሊያ፤ መግለጫ ነው፤” (ገጽ 988)። በሁለቱም ሊቃውንት አተያይ ውስጥ ፊደል የድምፅና የቃል ምልክት መሆኑን በአጽንዖት ተገልጧል።

ስለሆነም፣ እንደማንኛውም የሰው ልጆች ፈጠራና ቅርስ ከጊዜ ጋር ሊለወጥና ሊሻሻልም መቻሉን ጠቋሚ ሁናቴ በትርጓሜው ውስጥ አለ።

የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነን፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በአዲስ ታይምስ መጽሔት (ቅጽ 1፣ ቁጥር 6) ላይ ያወጡት “የአጻጻፍ ሥርዓታችንን ስለማሻሻል” የሚለውን ጽሑፋቸውን ካነበብን በኋላ ነው (ገጽ 14-15ና 26 ላይ ይመልከቱ)። ጽሑፉ በርካታ ቁምነገሮችን ይዟል። ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ስለፊደልና ስለአጻጻፍ ሥርዓታችን ጉዳይ ደግመው በዚህ ዘመን ላለውም አንባቢ ስላነሡትና የአንባቢያንን አስተውህሎትም ለመቆስቆስ ስለሞከሩ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በተጨማሪም፣ የሃሳቡን ማጠንጠኛ እንዝርትና ቀሰም በወጉ ስላቀረቡልንና የትኛውንም የሃሳብ ጎራ እንደሚደግፉም በአደባባይ ወጥተው ስለገለጹልን ላቅ ያለ ሥራ ሰርተዋል።

ዶ/ር በድሉ በጽሑፋቸው ውስጥ የሃሳብ ጎራቸውን ከመለየታቸውም በተጨማሪ፣ ሁለቱን “እምነቶቻቸውን” በጠራ ቋንቋ ገልጠውልናል። የመጀመሪያው እምነታቸው፣ ስለሞክሼ ፊደላት ጉዳይ ሲሆን፣ “አንድን ድምጽ ለመወከል ሲባል ሁለትና ከዚያም በላይ የሆኑ ሞክሼ ፊደላት መደጋገማቸው አስፈላጊ አይደለም፤” የሚል ነው። በሁለተኛ ደረጃም የጠቀሱት መከራከሪያቸው፣ “ጽሕፈትን/ፊደልን ለማሻሻል የሚገባው፣ ቋንቋ ከጊዜ ጋር እየተለወጠ የሚሄድ አኃዝ ስለሆነ ነው፤” ሲሉ ያቀርባሉ። በመጨረሻም፣ “የአንድን ቋንቋ የአጻጻፍ ሥርዓት ለማሻሻል ሲነሱ ሁለት ደረጃዎች አስፈላጊ ናቸው። እነርሱም፣ በመጀመሪያ የአጻጻፍ ሥርዓቱ ችግር አለበት ወይ ወይንስ “ብቁ” ነው በሚለው ላይ እንነጋገርበት፤” ሲሉ አንባቢያኑን ይጋብዛሉ። በማስከተልም፣ “በሁለተኛው ደረጃ ላይ ደግሞ፣ ፊደላችንና የአጻጻፍ ሥርዓታችን “ችግሮች አሉበት” የምንል ከሆነ፣ ችግሮቹ እንደምን ይስተካከሉ” የሚለው ነጥብ ላይ ኋላ እንመለስበታለን” የሚል ገንቢ ጥያቄ ነው ያነሱት።

የዶ/ር በድሉ ጽሑፍ ስለፊደላት ጉዳይ ሲያወሱ በአመዛኙ የሀገራችንን የፊደላት ክርክር ታሪክ ትተው፣ በውጭው (ማለትም በቱርክና በጃፓኖች) የፊደላት ለውጥ ጉዳይ ላይ አተኩረዋል። በተጨማሪም፣ በርካታ የፊደላትነ ለውጥ የሚደግፉ ንድፈ ሃሳቦችን በሰፊው አቅርበዋል። ይበል የሚያሰኝ ነው። ነገር ግን፣ የእኛን ጓዳም በተመለከተ በዝርዝር ስላልከለሱልን (ሙያቸው ነውና በቅጡ ያውቁታል)፣ ይህንን ጽሑፍ ለአንባቢያን እዝነ ሕሊና ይበጃል ስንል ጽፈነዋል። ስለፊደላችን ጉዳይም ጠቅለል ያለ መረጃ ለአንባቢያን ይሰጣል ብለን እናምናለን።

************************

የአማርኛ ፊደላትን ስለማሻሻል ልዩ ልዩ አማራጭ ሀሳቦች ከሃዳሲያን (ከተሃድሶ ፈላጊዎቹ) ሊቃውንት ዘንድ በይፋ መደመጥ የጀመረው ከዛሬ ሰማኒያ አመት ወዲህ ነው። (ቀደም ብሎ ግን ጉዳዩ በለሆሳስ ነበር የሚብላላው።) ለምሳሌ በዚሁ አርእስተ ጉዳይ ላይ ሀ) “መዝገበ ፊደላት ሴማውያት” ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ድሬ ዳዋ፣ በ1926 ዓ.ም.፤ ለ) “አዲስ የአማርኛ ፊደል” ከትምህርትና ሥነጥበብ ሚኒስቴር፣ በ1939 ዓ.ም.፤ ሐ) “ፊደልን ማሻሻል” ከትምህርት ወዳጆች፣ በ1940 ዓ.ም.፤ መ) “የአማርኛ ፊደል ሕግን እንዲጠብቅ ለማድረግ የተዘጋጀ ሪፖርት” በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት፣ ቅጽ 8፣ ቁ.-1፣ በ1962 ዓ.ም.፤ ሠ) “ስለአማርኛ ፊደል መሻሻል ጥናትና ውሳኔ” አ.አ፣ 1973 ዓ.ም. ተጽፈዋል።

መንግሥቱ ለማ (መንግሥቱ ለማ – ደማሙ ብዕረኛ (ግለ ታሪክ)) በሚል ርዕስ በ1988 ዓ.ም. በወጣው መጽሐፋቸው ላይ በ1940-1943 ዓ.ም. ስለነበረው የፊደል ክርክሩ ጭብጥ ሲያወሱ፣ “ከፊደል ይሻሻል ባዮቹ ይበልጥ፣ ፊደላችን በላቲን የአጻጻፍ ሥርዓት ይተካ፣ የላቲን ፊደላትም ሙሉ በሙሉ ፊደሎቹን ይተኳቸው የሚል ሃሳብ ያላቸውን፣ ከመቶ ዘጠና አምስቱ እጅ፣ ጣሊያን ተመልሶ ይግዛን እንደማለት ነበር የቆጠረው። ሆኖም ግን፣ መድረክ ላይ ተከራካሪ የነበሩት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ባለሥልጣኖች ስለነበሩ፣ ሕዝቡ ቆሽቱ ቢያርም ፈርቶ ዝም ብሎ ነበር፤” ሲሉ ያስታውሱታል (ገጽ 121)። ሆኖም፣ በባለሥልጣናቱ አካባቢ የነበረውን “ፊደል የማሻሻል ቀናዊነት” መንግሥቱ ለማ በአርምሞ ነው የሚያልፉት። በፊደሎቻችን አማካይነት የራሳችንን መጽሐፍት የማተሙ ፍላጎት በቤተ መንግሥት አካባቢ የተጀመረው ከአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት አንስቶ ነው። ባለሥልጣናቱም የዚያ “ሥልጣኔ” አቀንቃኞች ነበሩ።

ፊደሎቻችንን ለማተሚያ መሣሪያ እንደያመቹ ተደርገው መፊደሎቻችን መጽሐፍት የማተም ፍላጎት የተወጠነው በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት በ1513 ዓ.ም. ነበር። “ልብነ ድንግል ለፖርቹጋሉ ንጉሥ በጻፈው ደብዳቤው ላይ ግልጽ እንዳደረገው፣ “በፊደላችን መጽሐፍት መተም የሚችሉ” የእጅ ሥራ አዋቂዎችን ላክልኝ ብሎ ጠይቆት ነበር። ነገር ግን፣ የማተሚያ መሣሪያው ጉዳይ ከነገሥታቱ ሕሊና አልጠፋም ኖሮ፣ በአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት በ1887 ዓ.ም. ፈረንሳያዊው ደራሲ ሞንዶ ቪደልዬ በአፄ ምንሊክ ትእዛዝ ገዝቶ ማምጣቱን፤” (የፕሮፌሰር ሥርግው ኃብለ ሥላሴ፤ “አፄ ምንሊክ የአዲሱ ሥልጣኔ መሥራች”፤ በሚል ርእስ ማሳተሙት መጽሐፍ በገጽ 337 ላይ በዝርዝር ቀርቧል)። ሆኖም፣ የማተሚያ መሣሪያው ታትሞ ከመጣም በኋላ የፊደላችን ነገር ለመሣሪያው እንዲያመች ሆኖ መሻሻል ነበረበትና አፄ ምንሊክ ጉዳዩን በእጅጉ ገፍተውበት እንደነበር ፕ/ር ሥርግው ዋቢ ጠቅሰው ያስረዳሉ (ገጽ 370)።

ያነሷቸው ጥያቄዎች በከፊል ከዳግማዊ አፄ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ ቢያንስ በአራት ትውልዶች ተነስተዋል። አሁን ስንነጋገርበት እንግዲህ በአምስተኛው ትውልድ ዐይን፣ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። የመጀመሪያዎቹ ትውልዶች፣ ማለትም እነአፄ ምኒሊክ “ፊደላችን ለምስጢር መልእክትና ለቴሌግራፍ አጻጻፍ አልተመቸንም” ከሚል ሃሳብ ተነስተው ነበር። ስለሆነም፣ ፊደላችን በላቲን ሥርዓት ይተካ ሳይሆን፣ “ለሚስጢር መልዕክትና ለቴሌግራፍ መልዕክቶች መላላኪያ እንዲያመች ሆኖ ይሻሻል፤” የሚል መነሻ ነበር ግንዘቤያቸው። ጉዳዩን በብዙ ገፍተውበት የሚከተሉትን ፊደላት እስከ እርባታቸው ለማሻሻል ጥረት አድርገው ነበር።

(ምንጭ፣ ሥርግው ሀብለ ሥላሴ፤ አፄ ምንሊክ የአዲሱ ሥልጣኔ መሥራች (ዓ.ም. የለውም)፤ ገጽ 369)

ሁለተኛው ትውልድም የፊደልን ጉዳይ ያነሳው ከጣሊያን ወረራ ቀደም ብሎና በኋላም ባለው ዘመን ነበር። አብዛኞቹ ተሃዳሲያንም የቤተ-ክሕነት ሊቃውንት ነበሩ። “የነአለቃ ለማ ትውልድ” ብለን ልናወሳው እንችላለን። ይኼኛው ትውልድ ደግሞ፣ “የአማርኛ ፊደሎች ጊዜያቸው አልፏል፤ አርጅተዋል፤ አሮጌ ሆነዋል፤ አይረቡም፤ ለማተሚያ መኪናና ለቅልጥፍና አይመቹም” የሚል ክርክር ነበር ያነሳው። በአመዛኙ የቀዳሚውን ትውልድ ጥያቄ በቤተ-ክህነት ዙሪያ ሆነው እንደገና ለማራገብ ነበር የጣሩት። ስለሆነም፣ “የቅዱሳን ሰማዕታትና የፃድቃን ገድል የተጻፈበት ፊደል ካረጀባችሁ፤ ከጃጀባችሁ፤ ለምን ከሁለት ያጣ እንሆናለን። የግዕዙ ፊደል ይቅር ካላችሁ፣ ለምን የሙስሊም ወንድሞቻችን ለዘመናት የተጠቀሙበትን የአረቢኛ ፊደል አንጠቀምም። ምን የነጭ ፊደል ያዋውሰናል?!” የሚል ደገኛ ክርክር ነበር ያነሱት (መንግሥቱ ለማ – ደማሙ ብዕረኛ፣ 1988 ዓ.ም.፣ ገጽ 124)። ጉባኤው በአለቃ ለማ ሀሳብ ድንብርብሩ ወጥቶ ተበተነ።

ሦስተኛውም ትውልድ የዘመኑን ችግሮች ለመፍታት ጥሯል። ዋናው ችግር የነበረው፣ “ፊደላችን ለጽሕፈት መኪና (ለታይፕራይተር) የተመቸ አይደለም፤” የሚል ነበር። በዚህኛውም ትውልድ እንደመጀመሪያው ሁሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሚኒስትሮች ሳይቀሩ ጎራ ለይተው ተከራክረዋል። በዚህኛው ጊዜም ክርክሩ እጅግ የበረታ ነበር። በወቅቱ የጤና ጥበቃ ም/ሚ/ር አበበ ረታ፣ የጽሕፈት ሚ/ሩ ብላታ ዘውዴ በላይነህ፣ መርስዔ ሀዘንም ከ1943 ጀምሮ የጤና ጥበቃ ም/ሚ/ር ነበሩ። አቶ መኮንን ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ነበሩ። ኮለኔል ታምራት ይገዙም የትልቅ መኳንንት ዘርና ባለወገን ናቸው። በአንፃሩ ደግሞ፣ እነአቶ ብርሃኑ ድንቄና እነመንግስቱ ለማ ከካህናቱ ወገን ሆነው ነበር የሚከራከሩት። ከላይ እንዳልኩት፣ ይኼኛው ክርክር በሦስት ረድፍ ያሉ ተሟጋቾች ናቸው የተከራከሩበት። ፊደላችን በላቲን ፊደል ይተካ የሚሉት ወገኖች በነራስ እምሩ፣ በመርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስና በነታምራት ይገዙ አቀንቃኝነት ሲወከሉ፤ “የለም! ፊደላችን በላቲን አይተካም ግን ማሻሻል አለበት” የሚለውን ሃሳብ ደግሞ እነ ሚ/ር አበበ ረታና ብላታ ዘውዴ በላይነህ ነበሩ የሚያራምዱት። በሦስተኛው ረድፍ ያሉት ወገኖች ደግሞ መሠረተ ካህናት ስለነበሩና የፖለቲካ ስልጣናቸውም እስከዚህም ስለሆነ መድረክ ተነፍጓቸው ነበር። ዋና ዋናዎቹ ተከራካሪዎችም አቶ ብርሃኑ ድንቄ፣ የኔታ አስረስ የኔሰውና አቶ መንግስቱ ለማ ነበሩ። አቶ መንግሥቱ ከሁሉም በእድሜ ታዳጊው ወጣት ነበሩ (መንግሥቱ ለማ – ደማሙ ብዕረኛ (ግለ ታሪክ)፣ 1988 ዓ.ም.፣ ገጽ 115-124)።

ወደአራተኛው ትውልድና ወደፊደል ክርክሩ እንለፍ። ይህም ትውልድ የሀዲስ አለማየሁን “ፍቅር እስከ መቃብር” እያነበበ የተማረና በስነ ልሳን እውቀቱም ቢሆን ወደፊት የተራመደ ነበር። የዚህም ትውልድም ዋናው ችግር “የፊደሎቻችን ቁጥር በዛ፣ የሚክሼ ሆሄያት ድግግሞሽ ይቅር፣ የሚጠብቁና የሚላሉትን የማርኛ ቃላት በወጉ ካለየናቸው ተማሪዎቻችን ለማስተማር አስቸጋሪ ሆነውብናል፤” ከሚል ነበር። በአመዛኙ ከማስተማርና ከስነዘዴው ጋር የተያያዙ ችግሮችን ያማከለ ነበር። በዚህ ዘመን “የፊደል ሠራዊት” የሚባል የማንበብና የመጻፍ ትምህርት ለጎልማሶች ይሰጥ ስለነበር፣ የፊደል መምህራኑ ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸው ነበር። ለአብትም ያህል እነአቶ ሀብተ ማርያም ማርቆስ፣ በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ (መጋቢት 6ና 13/1961 ዓ.ም.) ላይ በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ሰፊና አስተማሪ የሆነ ጽሑፍ አውጥተው ነበር (ገጽ 5፣7 ላይ ይመልከቱ)።

አቶ ሀብተ ማርያም በጽሑፋቸው መቋጫ ላይ ሲደርሱም፣ “አጻጻፋችንን አሻሽለንስ? ከዚያ በፊት በተለመደው አጻጻፍ የተመዘገበው ጽሑፋዊ ቅርሳችንን ሁሉ ምን እናድርገው? ለመጪውስ ትውልድ እንዴት አድርገን ጽሑፋዊ ቅርሳችንን እናስተላልፈው? የታሪክንስ ክር ለመበጠስ መሞከር አይሆንብንምን?” የሚሉ ወገኖች በብዛት ይደመጣሉ ካሉ በኋላ፤ “በተለይም ንግግር ከጊዜ ጋር አብሮ የሚለወጥ ስለሆነ፣ ንግግሩ በተለወጠ ቁጥር ጽሕፈቱስ አብሮ ሊለወጥ ነው ወይንስ ምን ሊደረግ ነው?” ሲሉ ሞጋች ጥያቄዎችን ያነሳሉ። በመጨረሻው ላይም፣ “ብንስማማም-ባንስማማም፣ አጻጻፋችን ለብዙ ጊዜያት አሁን ባለበት ሁኔታ የሚቆይ ይመስላል፤” ሲሉ ተስፋቸውን ገልጠዋል (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ መጋቢት 13/1961 ዓ.ም.፣ ገጽ 7)።

በተመሳሳይ ሁናቴም፣ አቶ ከበደ ዮ. ቤርተሎሜዎስ የተባሉ መምህር “የአማርኛ ፊደልን ስለማሻሻል የቀረበ ጥናት” በሚል ርእስ ሥር ስለሚክሼ ፊደላትና እንደምን ሆነውስ ሊሻሻሉ እንደሚችሉ አጭር ቅኝትና አማራጭም አቅርበዋል። አብዛኛውም ሃሳባቸው ሄዶ ሄዶ ደራሲ/አምባሳደርና/ሚኒስትር ሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር መግቢያ ላይ ካሰፈሩት ሃተታ ጋር ተመሳሳይነት ያለው (ኧረ እንዲያውም ድጋፍ ነው፤) ሆኖ ይቋጫል (አዲስ አመን፣ ሰኔ 12/1961 ዓ.ም.፣ ገጽ 2)።

ይኼው የአራተኛው ትውልድ የፊደል ክርክር ሙሉ ለሙሉ ለአራተኛው ትውልድ ብቻ የተተወ አልነበረም። በተለይም የኔታ አስረስ የኔሰው ለዚህ ትውልድ ስለፊደል ምንነት በሠፊው ለማስተማር በማሰብ አራት መጽሐፍትንና አንድ የጋዜጣ ላይ መጣጥፍም አሳትመዋል። እነርሱም፣ ፍኖተ ሰላም (1940)፣ ፍኖተ ጥበብ ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአብሔር (1958)፣ የካም መታሰቢያ (1951)፣ ትቤ አኩሱም መኑ አንተ (1951) ሲሆኑ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ደግሞ “የአማርኛ ፊደል ክርክር” የሚል ሃተታ በነሐሴ 1/1955 ዓ.ም. አውጥተዋል። አስረስ በሁሉም ጽሑፎቻቸው ላይ ስለአማርኛ ጽሑፍ አመጣጥ ካወሱ በኋላ፣ እያንዳንዱ አማርኛ ከግዕዝ የተዋሰው ፊደል ስንት ድምጾች እንዳለው ሲመልሱ እንዲህ ነበር ያሉት። “የግዕዝ ፊደሎች 26 ናቸው። እነዚህም 26 ፊደሎች በ7ቱ አናባቢዎች ተባዝተው 182 ይሆናሉ። እነዚህም የፊደላት ብዜቶች የሚወክሉት የፍጥረታት መጀመሪያ ዕለት ከሆነው ከሚያዝያ 1 ቀን ዕለተ እሑድ ጀምሮ እስከ መስከረም 31 ቀን ዕለተ ቅዳም/ቅዳሜ ያሉትን 26ቱን እሑዶች፣ 26ቱን ሰኞዎች፣ 26ቱን ማክሰኞዎች፣ 26ቱን ረቡዑዎች፣ 26ቱን ሐሙሶች፣ 26ቱን ዐርቦችና 26ቱን ቅዳሞዎች የሚወክሉ ፊደሎች ናቸው እንጂ በዘፈቀደ የመጡ አይደሉም፤” ሲሉ ይከራከራሉ። ስለዚህም፣ እንደየኔታ አስረስ አስተምህሮት ከሆነ የአማርኛ ፊደሎች ድምጽን ብቻ የሚወክሉ ሳይሆኑ፣ ፤መለኮታዊ የሆነ ሚስጢርም” ያላቸው እንደሆኑ ያብራራሉ።

ሌላው የአራተኛው ትውልድ መለዮ የሆኑትን ሃሳቦች ማሳያው በ1956-1966 ድረስ የወጡት ጽሑፎች ናቸው። አንዱ ስለ”ቋንቋና ፊደል መሻሻል ጉዳይ” መነጋገር ይገባናል ሲል፣ ሌላው ወገን ደግሞ፣ “ፊደሉ ትተን ሌላውን ለማሻሻል እንሞክር፤” ሲል ያጣጥለዋል (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ሚያዝያ 3 ቀንና ግንቦት 15/1956 ዓ.ም.፤ አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 10ና መጋቢት 7/1961 ዓ.ም.)። በመጨረሻም፣ ከየካቲት 6-9 ቀን 1972 ዓ.ም. ድረስ በናዝሬት አዳማ ራስ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ተሰብስቦ-ስለአማርኛ ቋንቋ ፊደላት፣ ስለአማርኛ ሞክሼ ቃላት፣ ስለፍንቅጽ ሆሄያት፣ ስለስርዓተ ነጥቦችና ስለአማርኛ ቁጥሮችም ባለአስር ነጥብ ውሳኔ አሳልፎ ነበር። በጉባኤውም ላይ፣እነሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ አቶ አሰፋ ሊበን፣ አቶ አበበ ወርቄ፣ አቶ ሀብተ ማርያም ማርቆስ፣ አቶ መንግሥቱ ለማ፣ አቶ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ፣ አቶ ሠይፉ መታፈሪያ፣ ከዶክተሮቹም መካከል-ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፣ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ፣ ዶ/ር መርዕድ ወ/አረጋይ፣ ዶ/ር ብርሃኑ አበበና ዶ/ር አባ ገብረየሱስ ኃይሉ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በአብላጫ ድምጽም በዘጠኝ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስተላልፈዋል (ስለአማርኛ ፊደል መሻሻል ጥናትና ውሳኔ፣ አ.አ 1973 ዓ.ም.፤ ገጽ 45-48)።

ወደአምስተኛው ትውልድና ስለፊደል ጉዳይ ያሉትን ነጥቦች እናንሳ። ይህ ትውልድ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ያለውን ትውልድ ይመለከታል። የአማርኛ ፊደላት በግልጽ የፖለቲካና የፖለቲከኞችም አጀንዳ ሲሆኑ ባይኑ በብረቱ አይቷል። ብዙዎቹ የኩሽና የናይሎ ሰሃራ ቋንቋዎች ወደ ላቲን ፊደላትና የአጻጻፍ ሥርዓት ድርስም ብለው ሲነጉዱ ተመልክቷል። ስለሆነም፣ ስለፊደልና ስለአጻጻፍ ሥርዓታችን መሻሻል ሲነሳ በጥርጣሬና የሻጉራ ነው የሚመለከተው። ዞሮ ዞሮም፣ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕል፣ ሃይማኖትና ቅርስ ላይ የተቃጣ በትር አድርጎም ነው የሚያየው። ትውልዱ በእጅጉ የባዕዳን ተፅዕኖና የእጅ አዙር የባሕል ወረራ አንገፍግፎታል። ያንንም በኮሮጆ ውስጥ ድምጹን በመክተት፣ በአብያተ ክርስቲያናትና በቤተ መስጊዶችም ውስጥ በይፋ እየታገለው ነው። ባዕድ አስተሳሰብንና የባዕዳን ሴራ ነው ብሎ የተጠራጠረውን ሁሉ ጠልቆ ለመመርመር አይሻም። በደፈናው ይጠላዋል፤ ያጥላላዋል። ስለዚህም፣ የሕዝቡን ስስ ብልቶች በዘዴና በመላ መደባበሱ ነው የሚሻለው።

************************

የቋንቋ እድገት ወይም አጠቃቀም ከፊደልና ከአኃዝ ጋር ተያይዞ እንደሚጓዝ አይካድም። በተለይም፣ በዚህ የብዕር፣ የወረቀትና የመቀምር (የኮምፒውተር) ዘመን፣ ፊደል የሌለው ቋንቋ ሊያድግ ቀርቶ ሊኖርም አይችልም ይባላል። ስለዚህም ነው፣ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የላቲን ፊደሎችን ወደመዋሱና መጠቀሙ ያዘነበሉት። ከላይ እንዳልኩት አዲስ ነገር አላመጡም። በአለቃ ለማ ትውልድና በመርስዔ ሀዘን ትውልድ ጊዜ የነበረውን ሀሳብ ነው ለሥልጣኔና ለዕድገት ይበጃል ብለው ያደረጉት። ተደጋግሞ የሚነሳውም የቱርክ ፊደሏን ትታ የላቲን ፊደልን መቀበሏና የጃፓን ፊደሏን ሳትቀይር በሥልጣኔ የመገስገሷ ታሪካዊ ተሞክሮ ነው። የኛ አገር የብሔር ፖለቲከኞችና አመራራቸው የቱርኩ ልምድ ይሻለናል ብሎ ከወሰነ፣ ይኼው ሁለት አስርት አመታት ገደማ ተቀጠሩ።

ብዙዎቹ የሴም ቋንቋዎች በዚህ በኩል በጣም የታደሉ ናቸው። በተለይም አማርኛ እድለኝነቱ አያጠራጥርም። የራሱ ፊደል፣ ሥነ ጽሑና የራሱም አኃዝ (ቁጥሮች) አሉት (ማለትም ከግዕዝ የተዋሳቸው)። ያም የሚያኮራና የሚያስመካ ነው። ያም ሆኖ እክሎች ቢኖሩበት አያስደንቅም። እንደሌሎቹ የሰው ልጅ ሥራዎች ሁሉ ገና “ለፍጽምና” አልደረሰም። “ሆሄያቱ ለቴሌግራፍ መልዕክት ማስተላለፊያነትና ለጽሕፈት መኪና አጠቃቀም ያስቸግራሉ፤” የሚለው የአንደኛውና የሦስተኛው ትውልድ ጥያቄዎች ከኮምፒውተርና ከsoftwares መፈጠር ጋር ያከተሙ ጉዳዮች ሆነዋል። የአራተኛው ትውልድ ያነሳው ለማስተማር ያስቸግራሉና መሻሻል አለባቸው የሚለው ሃሳብም በቴክኖሎጂው ረዳትነትና በዘመኑ መንፈስ ተቃኝቶ መፍትሄ እንደሚያገኝ ተስፋ አለን።

የአማርኛ አኃዞች ለሒሳብ ሥራ አለመመቸታቸው እሚካድ አይደለም። ሌላው ቀርቶ የአማርኛ አኃዝን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር እንኳ ከባድ ናቸው የሚሉ ሊቃውንት አሉ። ስለዚህም ነው ይሄንን ከፍተኛ የሆነ የማንነት ጥያቄ ፈተና በለሆሳስ አልፈነው፣ የአውሮፓውን ቁጥር ለብዙ አሰርት ዓመታት በሂሳብ ማስተማሪያነት የምንጠቀመው። ይህም ቢሆን አያስገርምም፤ አያሳፍርምም። ፊደሎቻችንም ሆኑ አኃዞቻችን የተፈጠሩት ቴሌግራፍ፣ የጽሕፈት መኪናና የሒሳብ ስሌቶች ወረቀትና መቀምር ላይ መጻፍ ከመጀመራችን አያሌ ዓመታት በፊት ነው። ያን ጊዜ መሠረታዊ ትምህርት (የፊደል ሠራዊት) አጣዳፊ አጀንዳ አልነበረም። መማር የሚያስፈልገው ለቤተ ክህነት አገልግሎት ብቻም ነበር። እስከ ሰባና ሰማንያ ዓመታትም ድረስ፣ ሚሊዮን የሚባለው ቁጥር በኅብረተሰባችን መዝገበ ቃላት ውስጥም አልነበረ። (እነ”ሚሊዮን ነቅንቅ” የሚባሉት ስሞች የመጡት ከ1925 ዓ.ም. በኋላ ነው።) ቢሊዮንማ የታወቀውም በ1958/59 ገደማ እንደነበር አዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ማየቱ ብቻ ይበቃል። ከዚያ በፊት፣ “አንድ ቢሊዮን ለማለት ሲፈለግ አንድ ሺ ሚሊዮን፣” ነበር የሚባለው። ሚሊዮንና ቢሊዮን የሚባለው ሒሳብ በሕብረተሰባችን አኗኗር ውስጥ ያልገባ ስለነበረ ነው።

ምንጭ

ሰሎሞን ተሰማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)

One thought on “ሞክሼ የአማርኛ ፊደላት እና የባለሙያዎች ማብራሪያ ክፍል አንድ

Leave a comment