ቅዥት – ሄኖክ ስጦታው

ቅዥት

የህልም ዓለምን ሳካልል፣
በቁም ሳለሁ ተኝቼ
ከወደቅሁበት ፀሊም ዓለም፣
ሳልፈልገው ተገፍቼ፤
እንደ ሌሊቱ ቅዥቴ፣ መሮጥ ተስኖት እግሬ
ሳልፈልገው ተተብትቤ፣ እግር-ተወርች ታስሬ፤
ልክ እንደዚያው ቅዥቴ፣
በቁም ታፍኖ አንደበቴ
እንዳላመልጥ ከእስራቴ፣
በኖ ጠፋና ብርታቴ . . .

ዘመኔን በግድ ታቅፌ
በቃ እንዳልል ጋት አልፌ
ተወግቼ አንዳች መርፌ፤

ተውሰብስቤ በእልፍ ቅዥት
ስንቱን ዓለም አካለልኩት?!
መሬት ለመሬት ስንፏቀቅ፣
ሰማየ-ሰማያት ስንሳፈፍ
ድንገት መጋለብ ጀምሬ፣
ድንገት ባሕር ስቀዝፍ . . .
ስንቱን ዓለም አካለልኩት?!

የማላውቀው ፤ ግን ያየሁት
የምኖረው፤ ግን ያከልሆንኩት
የማፈቅረው፤ ግን ያጣሁት፤
የምመኘው፤ ግን ያልሆንኩት. . . !

ትላንት ቅዥት፣ ዛሬ ቅዥት
መዋል ቅዥት፤ ማደር ቅዥት፤ መኖር ቅዥት፣
ያሻሁትን ብቃዠውም፤
ቅዥቴን ግን አልኖረውም
የኖርኩትን አልቃዠውም!
መጋቢት፣ 28፣ 1999ዓ.ም
ሄኖክ ስጦታው ከ(ሀ-ሞት የግጥም ስብስብ መጽሐፍ፣ በቅርብ ቀን የሚወጣ)

“ትጠምቂልኝ ጀመር”

“ትጠምቂልኝ ጀመር”
ለጠላሽ መጥመቂያ፣ ጋኑን አጥነሻል
ብቅል አብቅለሻል፣ አሻሮ ቆልተሸል
ጌሾ ቀንጥሰሻል፣ እንኩሮ አንኩረሻል…
* * *
ተጠጥቶ ሳያልቅ፣ ከጋን ያለው ጠላ
ቅራሪው ሳይወጣ፣ ትጠምቂያለሽ ሌላ፡፡
* * *
ያን ሰሞን ሳልጠጣ
በፍቅርሽ ሰክሬ፣ ስምሽን ክንዴ ላይ-
በመርፌ ስነቀስ
በምናብ ስቃትት፣ በቅናት ስጠበስ
አንቺም አትጠምቂ፣ እኔም ጠላ አልቀምስ፡፡
የፍቅራችን እድሜ፣ በጨመረ ቁጥር
የጎሸ – ያልጎሸ፣ አንዳንዴም ፍሊተር
ጠላ በየአይነቱ፣ ትጠምቂልኝ ጀመር፡፡
ሄኖክ ስጦታው