ሐዘንሽ አመመኝ/ ደበበ ሰይፉ

ውል አልነበረንም የፍቅር ቀጠሮ
ቃልም አላኖርንም በወግ ተቀምሮ፤
እኔ አንቺን እንዳላይ
አንቺ እኔን እንዳታይ አምባችን ተቃጽሮ
ዕጣችን ተካሮ፤
ቀለምሽ ከዐይኔ አሻራሽ ከጣቴ ባይጠፋ ተማትሮ
(እትብት እምብርት ሁኖ እንዲኖር ደድሮ)
ይኸው አካሄደን በድንገት ዘንድሮ።
የገጽሽ ብርሃን ቢጠይም ፀዳሉ
ድምፅሽ ቢቀጥንብኝ ቢሠልብኝ ቃሉ
ወዘናሽ ቢማስን ዛሬ ያለውሉ
በእጆችሽ ጨበጠኝ ሐዘንሽ ሥዕሉ
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
ጀንበር ነሽ አበባ ሕይወት ተስፋ ዘቦ
ፋሲካ ዕንቁጣጣሽ ማኅሌተ ገንቦ
በዬ ያወደስኩበት ታዘበኝ ዘመኔ የትላንታት ቀኔ
ዛሬ ሊጮህብኝ ቅኔ እንዳይደል እውኔ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
የገደል ማሚቶን ታዘብኳት ተኝታ
በጩኽትሽ ማየል አኩርፋና ታክታ
ላንቃዋ ይታየኛል ደም ለብሶ ደም ጐርሶ
ቃልሽ ያለፈበት በጭንቅ ተለውሶ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
ጽጌሬዳይቱ ንቦችሽ አለቁ ሰዎችሽ ደቀቁ
ጨፌ ላይ ተኝተው ባድማ ላይ ነቁ፤
ዐዋይን ሰማኋት ስታለቅስ በይፋ
ከጐጆሽ ስትወጣ ትቢያዋን አራግፋ፤
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።
አላውቅልሽ ብዬ አታውቂልኝ ብዬ
እምነትሽን ጥዬ ፍቅርሽን ገድዬ
አኩርፌሽ ስቀመጥ ያው እንደ ባላንጣ
ይኸው ነጭ ማተብሽ ሊያስታርቀን መጣ፤
ሐዘን ነው ውበትሽ ውበት ነው ፍቅርሽ
ብርሃን – ጥለት አልቦ ከል ነጠላሽ
ዐይኔን የገለጠው ጥቁር ጨለማሽ፤…
ሐዘንሽ አመመኝ
ብሶትሽ ጠቀሰኝ።

—————–
ግንቦት 1966ዓ.ም.
ደበበ ሰይፉ

እኔ እወድሻለሁ /ገብረክርስቶስ ደስታ /ብዙ ሺህ ዘመናት
እልፍ አእላፍ ሌሊት
ሚሊዮን መሰለኝ
ፍቅሬ አንችን ስወድሽ ቀኑ ረዘመብኝ።
እኔ እወድሻለሁ
የሰማይ መሬቱን
የባህር ስፋቱን
የዓለም ዳርቻ የርቀቱን ያህል
እንደ ፅጌ-ረዳ
እንደ አደይ አበባ
እንደ ሎሚ ሽታ፡፡
እንደ እጣን ጢስ እንጨት፣ እንደ ከርቤ ብርጉድ፣
እኔ እወድሻለሁ፣
አበባ እንዳየ ንብ፡፡


እንደ ቢራቢሮ ጫካ እንደሚያስሰው
ፍቅርሽን በፍቅሬ በፍቅርሽ ልቅመሰው
ማር ወለላዬ ነሽ ከረሜላ ስኩዋር
አማርኛ አይበቃ፤
ወይ ጉድ!
ባለም ቋንቋ ሁሉ ቢወራ ቢነገር፣
እኔ እወድሻለሁ
እንደማታ ጀንበር።
እንደ ጨረቃ ጌጥ፣ እንደ ንጋት ኮከብ፣
እኔ እማልጠግብሽ
ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፡፡
ጡት እንዳየ ህፃን ወተት እንዳማረው
ጠጋ በይ ዘመዴ አፍሽ ህይወቴ ነው።
ጣይ እንዳየ ቅቤ
ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው፣
አፈር መሬት ትቢያ ውሃ እንደሚበላው፣
ፍቅሬ አንቺን ስወድሽ
ብዙ ሺህ ዘመናት
እልፍ አእላፍ ሌሊት
ውድ እወድሻለሁ፣
ዐይኖችሽን ባይኔ ተዳክሜ እያየሁ
ስወድሽ ስወድሽ
እኔ እወድሻለሁ።

16/9/1960ዓ.ም የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ
/ገብረክርስቶስ ደስታ/

የጉለሌው ሰካራም- በተመስገን ገብሬ

በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ፣ በአጭር ልቦለድ ምድብ የመጀመሪያው እንደሆነ በባለሙያዎች ድምዳሜ  አብላጫ ቦታ ያለው እና ኅዳር ፳፪ ቀን ፲፱፻፵፩ ዓ/ም የታተመው “የጉለሌው ሰካራም” ደራሲ ተመስገን ገብሬ የአማርኛው ውክፔዲያ  (ሪፖርተር ጋዜጣ እና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር) ምንጭ ጠቅሶ ካስቀመጠው ቅንጫቢ ታሪኩ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡
PDF FILE

 

ተመስገን ገብሬ የተወለዱት በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በደብረ ማርቆስ ከተማ በ፲፱፻፪ ዓ/ም ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የቤተ ክህነት ትምህርት ተከታትለዋል፡፡ ቤተሰባቸው ካህናት ከመሆናቸውም በላይ ጎበዝ ተማሪ ነበሩ። ጉብዝናቸው በዘመናዊ ትምህርት ሲከታተሉም ጎልቶ ወጥቷል፡፡ ከጎጃም አዲስ አበባም በመምጣት በስዊድን ሚሲይናዊ ትምህርት ቤት ተማሩ በወቅቱ ሀገሪቱ ካፈራቻቸው ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ተመስገን በጋዜጠኝነት ሙያ ከመሥራታቸውም በላይ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኃላፊነት ቦታ ተመድበው አገልግለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት በአርበኝነት ከጠላት ጋር ተፋልመዋል፡፡ በኋላም ወደ ሱዳን ተሰደው ገዳሪፍ ውስጥ እያሉ ኢትዮጵያዊያንን በልዩ ልዩ መልክ አስተምረዋል፡፡ ጣሊያን ከለቀቀች በኋላ የዘመናዊ አስተሳሰብና ዕድገት ዓላማዋ ዕውን እንዲሆንም ፍፁም የለውጥ አርበኛ ሆነው ሠርተዋል።
 
ተመስገን፣ ኅዳር ፳፪ ቀን ፲፱፻፵፩ ዓ/ም በ አዲስ አበባ ነፃነት ማተሚያ ቤት “የጉለሌው ሰካራም” በሚል ርዕስ ያሳተሙት ድርሰታቸው የመጀመሪያው፣ የታተመ የአማርኛ አጭር ልብ-ወለድ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የጉለሌው ሰካራም ከመታተሙ በፊት ስለ የካቲቱ ፋሺስታዊ ጭፍጨፋ (ግፊቱን በቀመሱት አርበኛው ደራሲ አገላለጽ፣ ‹‹ዓለም በድንገት ተለውጣ፣ አዲስ አበባም ኢጣሊያኖች ኢትዮጵያውያንን የሚያርዱበት ቄራ ሆና ነበር፡፡››) “የካቲት ፲፪” በሚል ርዕስ እና “ሊቀ-ጠበብት እውነቱ” የተሰኙ ሁለት አጫጭር ልብወለዶችን በጋዜጣ ላይ አውጥተዋል፡፡[1] ከዚህም ሌላ ‹‹ሕይወቴ›› የተሰኘውን ግለ ታሪካቸውን ያዘጋጁት አርበኛው አቶ ተመስገን ገብሬ በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ወረራ ጊዜም በደረሱት ‹‹በለው በለው አትለውም ወይ፤ የጥቁር አንበሳ አይደለህም ወይ›› በሚለው መዝሙራቸውም ይታወሳሉ፡፡
                      =================================================
 
የጉለሌው ሰካራም
በተመስገን ገብሬ
ክፍል ፩
በጉለሌ የነበረው የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ማነው ብለው ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሰፈር ለጠየቁ ሰዎች፤ ተበጀ ሰካራሙ
ተበጀ ዶሮ ነጋዴው፤ ተበጀ ነው ብለው ይነግሯቸዋል፡፡
የሕይወቱ ታሪክ ፍፁም ገድል ነው፡፡ ጢም ያለው ሽማግሌ ሰው ነው፡፡ ራሱን ጠጉር ውሃ ወይም መቀስ ነክቶት
አያውቅም፡፡ ማለዳ አይናገርም፡፡ በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ሲራገም ወይም ሲሳደብ ሲፈክር ወይም ሲያቅራራ
ድምጡ ከፈረንጅ ውሻ ድምጥ ይወፍራል፡፡ ቢያውቀውም ባያውቀውም ላገኝው ሁሉ ማታ ሰላምታ ይሰጣል፡፡
ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኝው ሁል ጋር ማታ ይስቃል፡፡ ቢውቀውም ባያውቀውም የሰላምታው አይነት እንደ ወታደር
ወይም እንደ ሲቪል ቢሆን ለእርሱ እንደተመቸው ነው፡፡ ከሰላምታው ጋር ድምጥ ትሰማለችሁ፡፡ ከአፉ ከሚወጣው
ከሚወጣው ግን አንድ ቃል መለየት አትችሉም፡፡
ቡን በተፈላ ጊዜ በጉለሌ በየምድጃው ሥር የሰካራም ተረት በየተጫወተ ሰው ሁሉ የተናገረ በተበጀ ላይ ነው፡፡ መልኩን
አይተውት ያላወቁት ባልቴቶች እንኳ ከፍንጃል ቡን ፉት እያሉየሌላውን ሰካራም ተረት በተበጀ ላይ ያላክኩት ነበር፡፡ይህ
እውነት ነበር፡፡ በጠባዩ ከተባለለት የባሰ ሰካራም ይሁን ወይም የጉለሌ ባህር ዛፍ ውስጥ ወጥቶ እንደ አዲስ እንግዳ ሰው
ሆኖ ለአዲስ አበባ ታይቷል፡፡
ከዱሮ የእንጨት ጉሙሩክ አጠገብ ወደ ምሥራቅ ሲል ሲል ካለው ወንዝ ማዶ ድልድዩን ወደ ምሥራው ተሻግሮ
መጀመሪያ የሚገኝው አነስተኛ ሳር ክዳን ቤት የተበጀ ቤት ማለት ያ ነው፡፡ በዚያ በቤቱ በዚያ በጉለሌ በሠፈሩ ኖረ፡፡
እንጨቱን ተሸክሞ አፈሩን ቆፍሮ ቤቱን የሰራው እርሱ ነው፡፡ ዋጋ ከፍሎ አስከድኖታል፡፡
ተበጀን ኩራት ተሰማው፡፡ ቆይቶ ደግሞ አይኖቹ እንባ አዘሉ፡፡ በጉንጩም የእንባ ዘለላ ወረደው፡፡ በግራ እጁ መዳፍ
ከጉንጩ የተንከባለለውን እንባ ጨፈለቀው፡፡ ዓይኖቹ እንባ ያፈሰሱ ለራሱ ጎጆ ስላለው ነው፡፡ ሊነገር በማይችል ደስታ ልቡ
ተለውስዋል፡፡
ዝናም ያባረራቸው ም ከቤቱ ጥግ ሊያጠለሉ ይችላሉ፡፡ ቤት የእግዚአብሄር ነውና ውዥብ እንዳያገኛቸው ከቤት ውስጥ
ዝናቡ እስኪያባራ ይቆያሉ፡፡ ተበጀን ‹‹ ቤትህን ይባርክ ›› ሊሉት ነው፡፡
እንግዲህ መንገደኛው ሁሉ ‹‹ ይህ የማን ቤት ነው ? ብሎ ሲጠይቅ የተበጀ ሊባል ነው ›› አለ፡፡
ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ ተበጀ የትኛው ነው ሲባል ዶሮ ነጋዴው ሊባል ነው ›› አለ፡፡
‹‹ ዶሮ ነጋዴው የትኛው ነው ›› ሲባል ያ የጉለሌው ሰካራም ሊባል ነው፡፡ አወይ፤ እኔ ተበጀ፤ ተበላሽቻለሁ አለና ደነገጠ፡፡
ከዚህ በኋላ ስለቤቱ ክብር እንኳ መጠጥ መተው ይገባኛል አለ ፡፡
መጠጥ ለመተው ያሰበበት የመጀመሪያ ጊዜው ይህ ነው፡፡ ሰካራምነት ጉዳት መሆኑ ተሰምቶት እንደሆን ይናገር ስለ ቤት
ክብር ማለቱ ግን ወደ ዳር ይቆይ፡፡ ስለ ቤት ክብር ምን ያውቃል? ዶሮ ነጋዴው ተበጀ ሰካራሙ ተበጀ አይደለምን ?
ሰካራሙ ተበጀ የሰራውን የገዛ ቤቱን ከፍቶ ገበና ኩራዙን አስቀምጦ ክብሪቱን ለመጫር ሲያወጣ በሐሳብ ተሰቅዞ እንደዚህ
አሰበ፡፡ መምረጥ አለብኝ፡፡ ከዚህ ቤት ያለው መጠጥ ሁሉ አንድ ሳይቀር እየወጣ ይፍሰስ፤ ከዚህ በኋላ ክብሪቱም ኩራዙም
በቤት ይደር፤ በአዲሱም ቤት ብርሃን ይዙርበት፡፡ አለዚያም በአዲሱ ቤት መጠጥ ይዙርበት፤ ኩራዙም ክብሪቱ ከቤት
ይውጣና ይፍሰስ፡፡ ሊደረግ የሚገባ ከሁለቱ አንዱ ነው እንጂ፤ በሰካራሙ ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት በአንድነት ይህች
ውሸት አለና ሳቀ፡፡
ከሁለቱ አንዱ ለማድረግ ሳይቆርጥ መብራቱን አቃጠለና ተቀመጠ፡፡ እንደገና ደግሞ እንደዚህ አሰበ፡፡ አያድርገውና ዛሬ
ሰክሬ ይህ ቤት ቢቃጠልብኝ አመዱን አይቶ በሰካራሙ ተበጀ ላይ ለመሳቅ ድፍን ጉለሌ ነገ ከዚህ ነው የሚቆም ! ጉለሌ ምን
ባለኝ? ወሬ ከማቡካት በቀር ጉለሌ ምን ሥራ አለው; ለአዲስ አበባም የስድስት ወር መሳቂያ በሆንኩ ነበር፡፡ መንገድ
አላፊዎችም ነገ በዚህ ሲያልፉ አመዱን አይተው ይህ የተቃጠለው ቤት የማን ነበር ሲሉ የተበጀ ሊባል ነው፡፡ በሰካራሙ
ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት ባንድነት ይህች ውሸት !
ወደ ውጭ እንደ እርም ወርውሮት የነበረውን የመጠጥ ጠርሙስ ሁሉ በጨለማው ዳብሶ አንድ በአንድ ለቃቀማቸው፡፡
አንዱን ግን ቀና አደረገና ከአፍንጫው አስጠግቶ አሸተተው፡፡ በጠርሙሱ ቅርፅ የመጠጡን አይነት አወቀው፡፡ ዊስኪ ነበርና
ስለዚህ ነው ሰው እንዳይሰማ ቀስ ብሎ የሳቀ፡፡ የጠርሙሱን ግማሽ ከጠጣ በኋላ ግን በአፉ ቡሽ ቢወትፍበት ለሳቁ መጠን
የለውም፡፡
‹‹ ጉለሌ ተኝቷልና ከዚሁ ከባሕር ዛፍ ሥር ቁጭ ብየ ብጠጣ የሚታዘበኝ የለም›› አለና አሰበ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ጉለሌስ
ተኝቶ ነበር ነገር ግን አሁን እርሱ ጠጥቶ የሰከረ እንደሆነ ጉለሌን ሊቀሰቅሰው ነው እርሱ ከጠጣ በጉለሌ ማን ይተኛል?
ጠርሙሱን ከከፈተው በኋላ ብርጭቆ ያስፈልገው እንደነበር ትዝ አለው፡፡ ሶስት የሚሆን ደኅና ጉንጭ ጠርሙሱን ከአፉ
አስጠግቶ ጨለጠ፡፡ ከዚያ በኋላ የሚጠጣበት ብርጭቆ ሊያመጣ አሰበ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሶስት ጉንጭ ምን ያህል
ጠርሙሱን ቀና አድርጎ በጨረቃዋ ተመለከተ፡፡ ‹‹ግማሹን ያህል ሰርጉጀዋለሁ›› አለና በሳቅ ፈነዳ፡፡ ‹‹ ለዚህችስ ብርጭቆ
ማምጣት አያሻም›› እያለ ጠርሙሱን አምቦጫቦጨው፡፡ በቀኝ ክንዱ መሬቱን ተረክዞ የቀረውን ጅው አድርጎ ወደ ውስጥ
ወረወረው፡፡ ባዶውን ጠርሙስ ደግሞ በጁ እየጠነቆለ ‹‹አንተን ደግሞ ለአንድ ዶሮ ለውጩ ሞያ እይዛለሁ የዊስኪ ቅርፍቱም
ዋጋ አለው አይጣልም›› አለ፡፡
‹‹እንዲሁ ሲጠጣ ሌሊቱን አጋመሰው፡፡ ቀጥሎ ከእግሩ በታች የወደቀውን ጠርሙስ እየቆጠረ ይህን ሁሉ እንደጠጣሁት
አላምንምና በጉለሌ አፈርሳታ ይደረግልኝ እነናቄ እነተሰማ አጎቴም ይጠጣሉ›› አለ፡፡
የጠርሙሱ መጠጥ ሁሉ እስኪያልቅ ድረስ ከዚያ ከዛፉ ሥር ተቀምጦ ያን ጠንካራ ትምባሆውን ከአፉ አላየውም፡፡ በሳቅ ጊዜ
ብቻ መልሶ ዝም እስኪል ድረስ መጠጡ ወይም ትምባሆው ከአፉ ያቋርጣል፡፡ የመጠጥና የትምባሆ ጊዜው ተበጀ ይህ
ነው፡፡ማለዳ በቀዝቃዛ ውሃ ታጠበ፡፡ ቋንጣም እንቁላልም ጠበሳና በዳቦ በላ፡፡ የጦም ቀን ነበር ‹‹ ለአባ ተክለ አረጋይ
አልናገርምና ነፍሴ ሆይ ግድ የለም አለ››፡፡ የነፍስ አባቱን ማለቱ ነው፡፡ ምናልባት በዓመት እንኳ አንድ ጊዜ ጠየቋቸው
ወይም ጠይቀውት አያውቁም፤ እርሱንም አያደርሰውም፤ እርሳቸውም ከበዓታቸው አይወጡም፤ አንዳንድ ጊዜ የዛሬውን
እሑድ ዕረፍት አደርገዋለሁ ያለ እንደሆነ እግሩን ደኅና አድርጎ የሚታጠብበት ቀን ማለት ነው፡፡
ደክሞት ነበርና ደኅና እንቅልፍ ተኝቶ ነበር፡፡ ዝናሙን ነጎድጓዱን ጎርፉን ውሃ ምላቱን አልሰማም፡፡ አንዳች ነገር ሰማ፡፡ ዘፈን
እና እልልታ የሰማ መሰለው፡፡ ትናንት ከጠጣው መጠጥ ኃይል መሰለውና ይህስ ዕብደት ነው እንጂ ስካር አይደለም አለና
ተመልሶ ተኛ፡፡
እንደገና አዳመጠ፡፡ የእርዳታ ጥሬ ጩኸት ሰማ፡፡ ከ አልጋው ዘልሎ ከወረደ በኋላ ቤቱን ለመዝጋት ጊዜ አላገኝም፡፡ በትልቁ
ወንዝ ዙሪያ ቁመው ይጮሁ የነበሩ ሰዎች የውሃው ምላት የሾገሌን ገረድ እንደጠለፋት ነገሩት፡፡ ጉርፍ የወሰደው ሾገሌን
ራሱን ቢሆን ወይም የሾገሌን ገረድ ለተበጀ ማዕረግ ምኑም አይደለም፡፡
‹‹ ገረዲቱን እናንተ በመጨረሻ ያያችኋት ወዴት ነው? ›› ብሎ ጠየቀና እየጠለቀ በዋና ይፈልግ ጀመር፡፡ ስለ ሾገሌ ገረድ
በትኩስ ውሃ ምላት ለመግባት አንሠዋም ያለው ጉለሌ በዳር ተሰልፎ ቁሞ ተበጀን ይመለከት ነበር፡፡
ብዙ ጠልቆ ከቆየ በኋላ ብቅአለና ‹‹ አገኝኋት መሰለኝ ›› ብሎ በዳር ላሉት ጮሆ ተናገረ፡፡ ለሰው ሁሉ ደስታ ሰጠው፡፡
ከሁሉም ይልቅ እርሱን ደስ አለው፡፡ የጠለቀውና የዋኝው ረጅም ጊዜ ስለሆነ ደክሞት ነበር፡፡ ነገር ግን ሊያወጣት
ይገባዋል፡፡ ጠለቀና አገኛት፡፡ በአሸካከሙ ላይ ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ አለዚያስ ውሃው ምላት እንደገና ይነጥቀዋል፡፡
እንደተሸከማት ውስጥ ለውስጥ ዋኝና ከዳር ብቅ አለ፡፡
ከሸክሙ ክብደት ኃይል የተነሣ ወዲያው ወደቀ፡፡ እርዳታ ተነባበሩለትና ጎትተው እርሱንም እርሷንም አወጧቸው፡፡
ተበጀ ተንዘራግቶ በብረቱ ውጋት እያቃተተ የጉለሌ ሰው በሳቅ ሲፈነዳ ሰማ- ከራሱ ነኩል ቀና አለና ‹‹ ሴትዮዋ ድናለች? ››
ብሎ በርኅራሄ ድምፅ ጠየቃቸው፡፡
አንዱ ቀረበና ‹‹ አሳማ ነው ያወጣሃው ›› አለው፡፡
የሚያቃትተው ተበጀ ከወደራሱ ቀና አለና ‹‹አሳማ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ‹‹ ለመሆኑ ከእናንተ ውሃ ወሰደባችሁ ሰው ነበር ወይስ
አሳማ ኑርዋል? ›› ብሎ ተበጀ ጠየቀና ያቃትት ጀመር፡፡
ጎረቤትህን እንደነፍስህ ውደድ ቢባልም ሰዎችን እነ እቲላን ነበር እንጂ የእቲላን አሳማዎች አልነበረም፡፡ እቲላ ጎረቤቱ አሳማ
አርቢ ነው፡፡ ውሃው ምላት ነጥቆ ወስዶ የነበረ የእቲላን አሳማ ሳለ ያላዩትን ቢያወሩ ግድ የሌላቸው ሰዎች የሾገሌን ገረድ
ውሃ ወሰዳት ብለው አውርተው የተበጀ ነፍስ ለአንድ አሳማ ነፍስ ሊያስለውጡት ነበር፡፡
መልካሙ የሰማዕትነት ሥራው ሁሉ ደግሞ እንዲሁ ርካሽ ሆኖ የሚቆጠር የሆነበት ዘወትር የሚሰክር ሆኖ ስለታወቀ ነው፡፡
በሞራልም (ግብረ ገብነት) መሠረት አደረግሁት የሚለውን ሁሉ ሳያውቀው እንደሚያደርገው ይቆጥሩበታል፡፡ ‹‹ በጎ ሥራህን ሁሉ በትኩስ መቃብር ውስጥ አፈር አልብሰው አንተ ሰው ሁን ሚስት አግባ ልጆች ይኑሩህ›› ይሉትና ይዘልፍት
ነበር፡፡
ድኃ ቢሆን ወይም ባለጠጋ ሰካራም ቢሆን ወይም ትኅርምተኛ ሁሉም የጉለሌ ልጆች ነን አባታችንም ጉለሌ ነው ብሎ ራሱን
ሚያኮራ እርሱ ተበጀ ብቻ ነው፡፡
ክፍል ፪
ከሚያሰክር ሁሉ ትኅርምተኛ ለመሆን ብዙ ጊዜ አስቦ ነበር፡፡ ሰክሮ ያደረበት ሌሊት አልፎ ብርሃን በሆን ጊዜ ከእንግዲህ
ወዲህ ‹‹መጠጥ አልቀምስም›› እያለ እየቀኑ በብርሃን ተበጀ ምለዋል፡፡ በነጋዉ የበለጠ ጠጥቶ የባሰ ሰክርዋል፡፡ ለመስከር
ይጠጣል፡፡ ደስ ያለው እንዲመስለው ይጠጣል፡፡ ብስጭቱን የሚረሳ መስሎት ይጠጣል ይህ ነው ተበጀ፡፡
‹‹ ይህን መስከርህን ካልተውህ ላንተ አበ ነፍስ አልሆንህም›› ብለው የመጀመሪያ ንስሐ አባቱ ብዙ ከመከሩት በኋላ መንፈሳዊ
ልጅነቱን ከርግመት ጋራ አስወግደውታል፡፡
ገረዶቹም ለርሱ ተቀጥሮ መሥራትን ከውርደት ቆጥረውት እየነቀፉት ሂደዋል፡፡ ‹‹ መጠጥ ካልተውህ አናገባህም›› ብለው
እየጊዜው ለጋብቻ ጠየቋቸው የነበሩ በቁመናው አሰናብተውታል፡፡ በሰምበቴ በማኅበርም ማኀበርተኛ ለቦሞን የጠየቃቸው
ነፍሱን ሳይቀር ንቀውታል፡፡
ይህ ሁሉ በእርሱ ዘንድ ከኢምንት አይቆጠርም፡፡ ያሉትን ቢሉ እርሱ ምን ቸገረው ገንዘብ እኮ አለው፣ ገንዘቡም ጥሬ ብር
ነው፡፡ ባለጠጋ ነው፡፡ መስከረም የባለጠጎች ነው፡፡ ትኅምርተኛ መሆንም የድሆች ነው፡፡ እንደ ልዩ አመፅ አድርገው ለምን
በእርሱ ይቆጥሩበታል? እንዲህ በተከራከረ ነበር፡፡
ነገር ግን ልዩነት አለው፡፡ እርሱ ብዙ ጊዜ ሰክሮ አውቶሞቢል በላዩ ላይ ሒዶበታል፡፡ ሰክሮ በበነጋታው ከእንቅልፉ ሲነቃ
ብዙ ጊዜ ከእስር ቤት ውስጥ አድሮ ራሱን አግኝቶታል፡፡ በጉለሌ መንገድ ዳር ባሉት በብዙ የውሀ ጉድጓዶች ሰክሮ
ገብቶባቸው እየተጮኸ ጉለሌ አውጥቶታል፡፡ ሰክሮ የጎርፍ ውሀ ከወሰደው በኋላ ብዙ ጊዜ እሳት አደጋ ደርሶለታል፡፡ ሰክሮ
ከቤቱ መድረስ እያቃተው ከወደቀበት ባቡር ምንገድ ሳይነሳ ብዙ ጊዜ ጎርፍ በላዩ ላይ ሲሄድበት አድርዋል፡፡
ይህ ሁሉ ውርደት እና ርክሰት ነው እንጂ ክብር ከቶ አይደለም፡፡ እንግዲያውስ ክቡር ደሃ ነው ገንዘብ ስለሌለው ራሱን
መግዛት ይችላል፡፡ ባለጠጋ ደግሞ መናኛ ተራ ነው፡፡ ገንዘብ ስላለው ራሱን መግዛት አይችልም፡፡ ይህን ሁሉ አሰበ፡፡ ስለኖረ
ባይማር እንኳ ብዙ ከማወቅ ደርሰዋል፡፡ ‹‹ ባለጠጋ ሆነ ወይም ደሀ፣ ሰው ከራሱ የበለተ መሆን ይገባዋል››፡፡ አለ፡፡
ቤቱን ከሠራ ከአምስት ወራቶች በኋላ ጀምሮ ተበጀ መጠጥ ከቶ አልተጠጣም ስለቤቱ ክብር መጠጥ እርም ነው ማለት
ጀምሯል፡፡ ያለፈውንም ዘመን መራርነት እያሰበ ተንገፍግፈዋል፡፡ አንድ ብሎ ለመጀመር ከወደቀበት ትቢያ አንስቶ ዕድሉን
ሲራግፍ እነደ ራዕይ ያያል፡፡
ያበላሸው እድሉ አሳዘነው ‹‹ በዚህ እድሜየ ሁሉ ሚስትም አላገባሁ ልጅም የለኝም›› አለና አዘነ፡፡ ውሾቹ እየተባሉ ሲጫወቱ
ተመለከተና ‹‹አመሌ ውሻ ነበርና ከውሾች ጋር ኖርኩ›› ብሎ ራሱን ረገመ፡፡ በውሾች ፈንታ አሁን በዚህ እድሜው ልጆቹ
ዙሪያውን እየተጫወቱ ሲፈነጩ ባየ ነበር እንዲሁ አሰበ፡፡
ቀልድና ወዘበሬታ ስለሚያውቅ እንደዚህ እያለ ይቀልድ ነበረ፡፡
ጉጃም የአበባውንና የግራር ማሩን ይጭናል፡፡ የተጉለትና የአምቦ ወረዳ ጌሾውን ያቀርባል፡፡ የሆላንድ የቢራ ፋብሪካ ቢራውን
ያወጣል የኢጣሊያ ፋብሪካ ወይን ጠጅ (ነቢት) ያፈላል፡፡ መደቅሳና ዘቶስ በግሪክ አገር ይጣራል በስኮትላንድ ዊስኪ
ይጠመቃል፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው በአራዳ የሚቀመጡትን እንዳይተማቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መዋሻዋ
እንደምትጮህ ጉጉት ሰካራሞች በከተማይቱ ይጮሃሉ፡፡
‹‹በደብረ ሊባኖስ ግን ድምጡን ዘለግ አድርጎ የሚናገር ወፍ እንኳ የለም፡፡ ውሃ እንኳ የሚጠጣ በመቅነኑ ነው፡፡ በአራዳ
አሁን ወይም በገዳም ምንም ገንዘብና ቢስቲን ለሌለው ውሀ ደግሞ እጅግ አድርጎ ይጣፍጣል፡፡›› ይህን የመሰለ ቀልድ
ይቀለድ ነበር፡፡
ሰካራሙ ተበጀ ግን ገንዘብ እያለው ወሀ ጣፍጦታል፡፡ ልዩ በሆነው በዚያ ማታ ወደ አልጋው ወጥቶ በተኛ ጊዜ መጠጥን
እርም ካደረገው አንድ አመት ከዘጠኝ ወር ከዘጠኝ ቀን እንደ ሆነው ጊዜውን ቆጥሮ አወቀው፡፡ ጊዜውንስ ማወቅ ለምን
አስፈለገው? ‹‹ እንደ ጉድፍ ( ጥንብ) መጣያ ትንፋሼ ተበላሼ፤ አፌም እነደ እሬት መረረኝ ሹልክ ብየ ዛሬ ብቻ፤ ጥቂት ብቻ፤
አንድ ጊዜ ብቻ፤ እኔ ብቻ፣ ብጠጣ ምን ይጎዳል›› ብሎ ተመኝቶ ስለመበረ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ አልጋው ወጥቶ ተጋደመ
ከተጋደመም በኋላ ተነሥቶ መጠጥ ቤት ለመሄድ ከባድ ከነበረው እንቅልፉ ለበላቀቅ ታገለ፡፡
በመጨረሻ ወደ መጠጥ ቤት በሄደ ጊዜ በውኑ ወይንም በሕልሙ እንደነበረ ራሱን ተበጀ አላውቀውም፡፡
የጠጣም እነደሆነ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ይደረግ በነበረው የአረመኔ ቅጣት እጁን እግሩ ከመቆረጥ ይደርሳል ብሎ
አላሰበም፡፡ አናጢ የጠረበው እንጨት ከቅልጥሙ ይቀጠላል ብሎ ክፉ ሕልም አላለመም፡፡ አንድ ሰካራም አንካሳ በአንድ
ዓመት ስንት የእንጨት እግር ይጨርሳል ብሎ ስለዋጋው አልተጨነቀም፡፡ ደኅና ምቾት ያለው አንካሳ ለመሆንም ገንዘብ
ያስፈልጋል፡፡
አንካሳው ሰው ሰካራም እንደሆን በእንጨት እግሩ በሰላም ጊዜ ይሄድበታል፡፡ በሁከት ጊዜ ደግሞ ይማታበታል፡፡ ሲማታበት
ይሰበራል ሲሰበርም ሌላ የእነጨት እግር መግዛት ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ የእንቸጥ እግር የሚሰሩ አናጢዮች ለደንበኞቻቸው
ትርፍ መጠባበቂያ እግር በሜንጦ ሰቅለው ያስቀምጡላቸዋል ይባላል፡፡ ተበጀን እንደዚህ ያለ ሕይወት አያጋጥመውም፡፡
በበቀለች ዓምባ_ መጠጥ ቤት ደረጃውን ተራምዶ ተበጀ በገባ ጊዜ የጥንት ወዳጆቹ ስካሮች በእቅፍ ልይ ተነባበሩ፡፡
እንደተወደደ መሪ በጫንቃቸው ላይ ተሸክመው እየተቀባበሉት በዕልልታ ጮሁ፡፡ ከመጠጥ ቤት ጠፍቶ የነበረው
ተመልሰዋልና በስካሮች ሁሉ ዘንድ ደስታ ሆነ፡፡ እንኳን በደኅና ገባህ! የመጠጥ ጠርሙሶቹን እንደ ዘንባባ ይዘው ተቀበሉት
ቁማርተኛው ያረጀ ግሪክ እየሳለ ተናገረ ሁሉም በደስታ ይጮሁ ስለነበረ አንድም የሰማው የለም፡፡
ረስቶት የነበረው መጠጥ ጣዕሙን ገና ሳያውቀው ገና ከጫብቃቸው ሳይወርድ በጩኸቱም በመጠጡም ተበጀ ሰከረ፡፡
ከጫንቃቸው ወደ ቁልቁል ጣሉት ፡፡ የሕፃንነት ዘመን አልፉልና ራስህን ችነል መሄድ ይገባሃል አሉት፡፡ ሰማህ? አቅም
አንሶህ መሄድ አቅቶሃልና እንደኩብኩባ እየዘለለህ መሄድ ትችል እንደሆነ ምርኩዜ ይኸውልህ ብሎ አንካሳው በየነ
አቀበለው፡፡ ምረኩዙን ለመያዝና ለመጨበጥ እጁን ሲዘርር በግምባሩ ከበሬት ላ ተደፋ፡፡ እንደ ወደቀም ሳለ፤ እስኪነቃ
ድረስ በመካከሉ ስንት ሰዓት አልፎ እንደነበረ ለማስተዋል አልቻለም፡፡
የመጠጥ ቤቱ እመቤት ጊዜ አልፏልና ከውጭ ጣሉትና ቤቱን ዝጉት ብላ አዘዘች፡፡
ወደቤቱ የተመለሰ መስሎት ሄደ፡፡ ማወቅ አልቻለምና ወዴት እንደሄደ ግን አላወቀም፡፡ አንድ መንገድ ሲያቋርጥ ተሰናከለና
ወደቀ፡፡ ከወደቀበትም ምድር ላይ በዳሰሰ ጊዜ ለእጁ የገጠመው የባቡር ሀዲድ ነው፡፡ ቤቱ ያለ በጉለሌ ነው፡፡ የሰከረበት
ደግሞ የበቀለች መተጥ ቤት ነው፡፡ መጠጥ ቤቱም ከዩሃንስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ምን ያህል ቢክር ነው የጉለሌ
መንገድ ጠፍቶት እስከ ባቡር ሀዲድ ድረስ ተሳስቶ የሄደ; ራሱን ይዞ ለመጮህም ራሱ ወዴት እንዳለ ማወቅ አቃተው፡፡
እንደ ቤቱ መንገድ ጠፋበት፡፡
ጥቂት መስማት ከቻለ በኋላ ጩኸት በስተ ኋላው የነፋ ነበረ የእሳት አደጋ ወይስ ባቡር ኑርዋል; እያፎደፎደ ሲሄድ ከወደ
ኋላው በኩል ምን እንደገፋው አላወቀም፤ ከኋላው በኩል ትልቅ ሀይል መታው፤ ከፊቱ በኩል ቀበሮ ጉድጓድ ተቀበለው፡፡
እግሩ እንደ ብርጭቆ ነከተ፡፡ ከወደቀበትም ሌሊቱን ሁሉ ደም ከእግሩ ዘነመ፡፡ ትንኝም እንደ ንብ በላዩ ሰፎ ደሙን
መጠጠው፡፡
ቀና ብሎ በአጠገቡ የወደቀውን የአህያ ሬሳ አሞራዎች ሲግጡት አየ፡፡ የቀረው ልቡ በድንጋፄ ተመታ የእርሱ እድል ከአህያው
ሬሳ ዕድል ቀጥሎ ሆነ፡፡ በስካሩ ምክንያት እስከ ዘላለም ድረስ ከአህያ ሬሳ እንደ ማይሻል ተረዳው፡፡ ነገር ግን የአሁኑ
መረዳት ለምን ይበጀዋል? ማወቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ አልፏል፡፡
በሕይወቱ ሳለ እንደ ወደቀ ያህያ ሬሳ መነሳትአልቻለምና በተራው አሞራዎቹን ዓይኑን ሊመነቁሩት ነው፡፡ ሥጋውን በልተው
ከጨረሱት በኋላ አጥንቱን ሊግጡት ነው፡፡ሌሊት ደግሞ ቀበሮዋች ሊረፈረፉበት ነው፡፡ ይህን እንዲያመልጥ ለመሸሽ
ከወደቀበት ሊነሣ እቃተተ ሞከረ፡፡ ባልተቻለው ጊዜ ግን ተጋደመ፡፡
በደሙ ላይ እነደተጋደመ አራት ቀኖች አለፉ፡፡ እግሩ እንደቀረበታ ተነፋ፡፡ እንደ ቅጠልያ ያለ እዥ ወረደው፡፡ ከወደቀበት
ያነሳው የመንግስት አምቡላንስ ባገኝው ጊዜ ፈፅሞ በስብሶ ነበር፡፡
ዶክቶር ክሪመር ባዩት ጊዜ ከሰማይ በታች ሊደረግለት የሚችል ሕክምና ምንድር ነው; ደሙ አልቅዋል፡፡ በሽተኞችን
ለመርዳት በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች የተለገሰውን ደም ለሚሰክር ጥጋበኛ አልሰጥም፡፡ እርሱን መንካት መርዙን ያስፈራል
ከዚህ በፊት ይህ እንዳይደርስበት እንዳይሰክር ብዙ አስጠንቅቀነው ነበር አሉ፡፡
ከንፈሩ ተንቀሳቀሰ፡፡ ላብ በፊቱ እንደ ውሀ ፈሰሰ፡፡ ለመናገር ጣረ፡፡ በመጨረሻ ግን መናገም ስይሆንለት ቀረ፡፡
ሐኪሞችም የገማውን ልብሱን ገፈፉት፡፡ እንደ ቅባትም ያለ መድኃኒት ቀቡት፡፡ ከግማሽ ሊትር የበለጠ ደም ሰጡት፡፡
በመጠጥ ከተጉዳው ከልቡ ድካም የተነሣ ኤተር ለመቀበል አለመቻሉን ከተረዱ ዘንድ የሚያፈዝ መድኃኒት ጀርባውን
ወግተው ሰጡት፡፡
አንዱ ሐኪም ከጉልበቱ ይቆረጥ አለ፡፡
ሌላው ግን ሁለተኛ እንዳይሰክር ከቂጡ አስጠግቼ እቆርጠዋለሁ አለና ከቂጡ አስጠግቶ ቆረጠው፡፡ የተቆረጠውን እግሩን
ከፊቱ መዝናችሁ አስታቅፉት ብሎ አስታማሚዎችን አዘዘ፡፡
እግሩን ከፊቱ መዘኑትና አሥር ኪሎ የሆነው እግርህ ይኸውልህ ታቀፈው ብለው አስታቀፉት፡፡
በዚህ ጊዜ በአጥንት የተጣሉት ውሾች በላዩ ላይ ተረፈረፉበትና በድንጋፄ ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ ይህ ሁሉ የደረሰበት በሕልሙ
እንደነበር ማወቅ አቃተው፡፡ ከአልጋው ላይ ወረደና ገረዱን ወይዘሮ ጥሩነሽን ከመኝታቸው ቀስቅሶ እየጮኸና እየተንዘረዘረ
ስንት እግር ነው ያለኝ ብሎ ጠየቃቸው፡፡
ወይዘሮ ጥሩነሽም ‹‹ድሮ ስንት እግር ነበረዎ ጌታ?›› ብለው ጠየቁት፡፡
እየጮኸ ሶስት ጊዜ ‹‹ ሁለት ሁለት ሁለት ነበረኝ›› አላቸው፡፡
ሶስት ጊዜ ሁለት ስድስት ማለት ነው፡፡ ልጆቼን ያሳደገች ላም ካራት እግር የበለጠ አልነበራትም ሰለዚህ የእርስዎም እግሮች
አራት ናቸው አሉት፡፡
‹‹የምሬን ነው የምጠይቅዎት;›› አለና ጮሆ ተንዘረዘረ፡፡
‹‹በእርግጥ ሁለት እግሮች አሉዎት ጌታ›› አሉት፡፡
ተበጀ እግሩን አጎንብሶ ለመሳም ሞከረና ራቀው፡፡ ወደ ሰማይ እያየ መጠጥ ማለት ለእኔ ሞት ማለት ነው አለ፡፡ ጊዜውም
ሌሊት ነበር፡፡
እንደዚህ የማሉበት ሌሊት ያልፋል ብለው ወይዘሮ ጥሩነሽ መለሱለት፡፡
——————————————————–

የፒ.ደ.ኤፍ ምንጭ http:// zelalemkibret.files.wordpress .com ላቅ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ

ይድረስ ለወንድሜ ለማላውቅህ

(ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን)

ይድረስ ላንተ ለማላውቅህ
ለወንድሜ ሩቅ ለማልፍህ
ለምታውቀኝ-ለማላውቅህ፥ ለምታየኝ-ለማላይህ. . .
ማነህ ባክህ?
ሳትወደኝም ሳታምነኝም፥ አጢነህ ለምትፈራኝ
ስናገርህ አጠንቅረህ፥ አተኩረህ ለምትሰማኝ….
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፥ ለአረህ ዟሪው ለገታሩ
ለሩቅ ገጠሬ ነባሩ
ለማላውቅህ ለዳር ዳሩ፥….
ማነህ


ከሩቅ የምታስተውለኝ
የማልለይህ-የምትለየኝ
ተግተህ የምትገምተኝ፥ ያላየኸኝ አስመስለህ
አቀርቅረህ ተግ ብለህ
ባንደበትህ የእርግማን መርዝ፥ በልብህ ትእዝብት ቋጥረህ…
የፀጥታው የዋሻው ሱቅ
ማነህ አንተ የቅርቤ-ሩቅ
ማነህ….
ከረን ነህ መለሎ ብሌን
ከአሰብ ወደብ እስከ ስሜን
ስትሳብ ስትሰበሰብ
ሽንጠ ሰንበሌጠ-መርገብ
ከኡመ-ራ ነህ ከመረብ
አኑአክ ወይስ ገለብ
ከዘር ተገፍተህ ተሰደህ
በሐሩር ሰደድ ተጥለህ
በንዳድ መቀመቅ ታጥረህ
በእልቂት አፋፍ ፈፋ ያለህ
ማነህ
‘አጋው’ ነህ ወይስ ሺናሻ
ቅማንቴ ነህ ወይ ፈላሻ
ስምህ የሆነብን ግርሻ፥
ግራ ጐንደር ነህ መተከል
ባላዋቂ የምላስ ቅርስ፥ የዘር ንፍገት ስትቀበል
ያለዕዳህ ስምህ ሲበከል
እምትችል እምትቀበል፥ እማትሞት እማትነቀል
ማነህ
ቆለኛ ሸክላ ሠሪ ነህ
ያገር ዕድል ያገለለህ።
ለጥበብህ እንደመካስ
በደባትር ትንታግ ምላስ
ዘለዓለም ልብህ የሚላስ
ማነህ
ገባር ነህ የሙክት ሳቢ
እረኛ ነህ የከብት አርቢ
አራሽ ነህ ያገር ቀላቢ
አማል ነህ የግመል ሳቢ….
ባክህ ማነህ ወንድምዬ፥ አንድም ቀን የማንወያይ
በውል፥ በጣይ፥ ባደባባይ
በፎቶ ግራፍ ዓይን እንጂ፥ ዓይን ለዓይን የማንተያይ
እኔ ለወሬ አንተን መሳይ፥ አንተ ለጭንቅ እኔን መሳይ።
ማነህ እኮ የማላውቅህ
ማዶ ለማዶ ሩቅ ለሩቅ፥ በመኪና ዓይን የማይህ
የማትቀርበኝ የማልቀርብህ
ጠረንክን የምጠየፍህ
በጋዜጣ በመጽሔት፥ ወሬህን የምተርክህ
ሥዕልክን ፎቶግራፍክን፥ ላገር ጎብኚ የምሸጥህ፥
ማነህ አንተ ወንድምዬ፥ የማላውቅህ የምታውቀኝ
ሶዶሬ ማዶ እምታልፈኝ
በዝምታህ የምትከሰኝ
ባይንህ ጦር የምትገሥፀኝ
የሆድክን የማልጠይቅህ፥ የሆድክን የማተነግረኝ፥
ማነህ
ቦረን ነህ አባ ጋናሌ
የኛዻ ጠር አባ ጣሌ
ወይ ‘ሳፋር’ ንጥረ ሶማሌ፥
ከረን ነህ ወይስ ዳንካሌ
አፋር ነህ አባ ቱማታ
ማታሐራ ወይ ከምባታ
ወይስ ኩናማ አባ ዱታ፥
ማነህ ጐበዝ ማነህ አያ
ኢማኑ ነህ አባ ራያ
ወይስ ኢቱ አባ ሎቲ
የአዳል ሞአ የአዳል ሞቲ፥
እኮ ማነህ ሩቅ ያለኸው
ማንነትክን የማላውቀው
እማልሰማ እማልጠይቅህ
እማትነግረኝ እማላውቅህ፥
ማነህ ጐበዝ ላስተውልህ፥ አተኩረህ ጭጭ እምትል
እማትጣጠፍ ቅምጥል
መሃል አገር ያልሸተተህ
ባሻገር ዙር ድንበር ያለህ
የእህል ደላላ እሚበላህ
ባለሚዛን እሚያዋካህ፥
ማነህ
የዝምታ መደብር ነህ?….
እኮ ማነህ ስምህ ማነው
የዘር ግንድህ የሰየመው
ተበጥሶ ያልተቀጠለው
ሥርህ ማነው?….
በልቦናህ የምታማኝ
ታዝበህ የምትሰማኝ
ባትወደኝም ባታምነኝም፥ አጢነህ የምትፈራኝ
ማክበር እንጂ እማታስጠጋኝ፥
ማንነትክን ምንነትንክን፥ ላልሰማህ የምጠይቅህ
ለጉልበት ለላብህ በቀር፥ ላንተነትህ የማልቀርብህ
ከዓይነ-ጥላዬ እምትሸሸኝ፥ ከዓይነ-ጥላህ እማልርቅህ
ላፌ እንጂ ለልቦናዬ፥ የማትመስለኝ የማልመስልህ
ከመንፈሴ እምገልልህ
ከሕሊናዬ እማሸሽህ
ቦታህን የማትረሳ፥ ቦታህን የማስታውስህ….
ማነህ
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፥ ሕመምከን ለማታዋየኝ
በጸጥታህ ለምትወቅሰኝ
ጐፈሬህን እንደአባትህ፥ እንደሞያህ አጐፍረህ
በወለባ አንቆጥቁጠህ
ሎቲ አጥልቀህ ጦር አንግበህ
በመኪና እግር እማልፍህ
የማትጠራኝ የማላውቅህ፥
ማነህ
በየቱሪስቱ ካርድ ላይ
ከቦህ ሰማያዊ ሰማይ
አተኩረህ የምትታይ
ውሸትክን ፈጠህ ሳቅሁ ባይ፥
እንደቴክኖክራሲ አግቦ
ዙሪያህ በሀሰት ጌጥ ታጅቦ
እፎይታ ያቀፈህ መስለህ
ትእዝብት በዓይንህ ጦር አዝለህ
ርቀህ ተቀብረህ ሰንብተህ
የቱሪስት ካርድ የሳበህ
አንተ ማነህ?
እኮ ማነህ ወንድምዬ፥ ደራሲ የሚቀኝብህ
ሠዓሊ የሚነድፍብህ
ቀሲስ የሚቀሰስብህ
የቱሪስት የጋዜጠኛ፥ ካሜራ እሚጋበዝብህ
የሚተች የሚተረጉም፥ የሚነድፍህ የማንም እጅ
የማነህ ደም የማነህ ቅጅ?….
አንተ የማማ ኢትዮዽያ ልጅ
እኔማ ሆኜብህ ፈረንጅ
አሳብ ለአሳብ ለተጣጣን
ምን አጣላን ማን አጣላን
ማን እንዳንወያይ ገራን
እንደባቢሎን ኬላ ግንብ፥ ለመተላለፍ የቀባን
አንተን የዘልማድ ዘላን፥ እኔን የመኪና ዘላን
እንድንሆን የገፋፋን?
ማነው ምንድነው ወንድሜ፥ ሆድ ለሆድ የሚያናክሰን
ሳንርቅ የሚያራርቀን፥ ሳናኮርፍ የሚያኳርፈን!….
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፥ ለምትሳብ ናዳ ጥጉን
ፈፋ ዙሪያ ሸንተረሩን
ሸለቆውን ፈረፈሩን
ዳር ድንበሩን ሩቁን-ሩቁን፥
ከዘር ተገፍተህ ተሰደህ
በሐሩር ሰደድ ተጥለህ
በንዳድ መቀመቅ ታጥረህ
በእልእቂት አፋፍ ፈፋ ላለህ….
እኛ መሀል ለሌለኸው
ታሪክህ ለተሸፈነው
ሁሉን ከሩቅ አብሰልስለህ፥ አጠንቅረህ ለምታየው….
ይድረስ ለክቡር ወንድሜ፥ ለምታየኝ ለማላይህ
ለምታውቀኝ ለማላውቅህ
ማነህ ባክህ….
ማነህ

ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን(እሳት ወይ አበባ)

(ለበጌምድር ወይጦ ባላገር – (1963፲፱፻፷፫ – ደባርቅ)

ወንድ ብቻውን ነው እሚያለቅስ

   ጸጋዬ ገብረ መድኅን
ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ      
ተሸሽጎ ተገልሎ፥ ተሸማቆ ተሸምቆ
ከቤተ-ሰው ተደብቆ
መሽቶ፥ የማታ ማታ ነው፥ ሌት ነው የወንድ ልጅ እንባው
ብቻውን ነው የሚፈታው፡፡ . . .
ብቻውን ነው የሚረታው፡፡ . . .
ችሎ፥ ውጦ፥ ተጨብጦ፥ ተማምጦ ተጣጥሮ
በሲቃ ግት ተወጥሮ
እንደደመና ተቋጥሮ
እውስጥ አንጀቱ ተቀብሮ . . .
መሽቶ፥ ረፍዶ፥ ጀምበር ጠልቆ
የጨለማ ድባብ ወድቆ
በእንቅልፍ ጥላ ሲከበብ፥ በዝምታ ሲዋጥ አገር
ፍጡር ሁሉ ተስለምልሞ፥ ብቸኝነት ብቻ ሲቀር . . .

የኋላ የኋላ፥ ማታ
ምድር አገሩ በእፎይታ
ዓይኑን በእንቅልፍ ሲያስፈታ
ሁሉ በእረፍት ዓለም ርቆ፥ ብቸኝነት ብቻ ሲቀርብ
ያኔ ነው ወንድ ዓይኑ የሚረጥብ
የብቻ፥ እንባ ወዙ እሚነጥብ፡፡
ብቻውን ነው፥ ብቻውን ነው . . .
የእንባ ጭለማ ለብሶ ነው
ወንድ ልጅ ወዙ እሚነጥበው፡፡
ዕጣውን ለብቻው ቆርሶ
ብቻውን ሰቀቀን ጐርሶ
ብቻውን ጭለማ ለብሶ
ገበናውን ሣግ ሸፍኖ
ክብሩን በሰቆቃ አፍኖ
ሌሊት፥ የማታ ማታ ነው
ሕቅ እንቁን እሚነጥበው
ኤሎሄውን እሚረግፈው . . .
ከዓይኑ ብሌን ጣር ተመጦ
ከአንጀቱ ሲቃ ተቆርጦ
ደም አልሞ ፍም አምጦ
ከአፅመ-ወዙ እቶን ተፈልጦ
ከአንጀቱ ሲቃ ቆርጦ
ደም አልሞ ፍም አምጦ
ከአፅሙ ወዙ እቶን ተፈልጦ
እንደጠፍር-ብራቅ እምብርት
እንደእሳተ ገሞራ ግት
‘ርቅ ነው ወንድ ልጅ እንባው
ደም ነው፥ ፍም ነው እሚያነባው፤
ንጥረ ሕዋስ ነው ሰቆቃው
ረቂቅ ነው ምሥጢር ነው ጣሩ፥__ብቻውን ነው የሚፈታው፥
ብቻውን ነው የሚረታው፡፡
ችሎ፥ ውጦ፥ ተጨብጦ፥ ሰቀቀኑን በሆዱ አጥሮ
በአንጀቱ ገበና ቀብሮ
ውሎ ጭጭ እፍን ብሎ፥ እንደደመና ተቋጥሮ
ጣሩን ውጦ ተጣጥሮ
በሲቃ ግት ተሰትሮ፥ . . .
ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ
ከቤተ-ሰው ተደብቆ
አንጀቱን በአንጀቱ ታጥቆ፥
ተሸሽጎ ተከናንቦ፥ ተሸማቆ ተሸምቆ . . .
የብቻ ብቸኝነቱ፥ የጭለማ ልብሱ እስኪደርስ
በዓይን አዋጅ ሃሞቱ እንዳይረክስ
ቅስሙ በገበያ እንዳይፈስ
ተገልሎ በእኩለ-ሌት፥ ወንድ ብቻውን ነው እሚያለቅስ፡፡
ጸጋዬ ገብረ መድኅን
እሳት ወይ አበባ
            ለዘውዴ ሸዋሞልቶት – (፲፱፻፶፭ – አምቦ – ኮልፌ)

እግር እንይ! (ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን)

poem in pdf
እግር እንይ!
(ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን)
አርቀን ማስተዋል ማለት፣ የኛን ሥልጣኔ ድልድይ
እግር ማየት ነው ብለዋል፣ እስቲ እንግዲህ እግር እንይ!
            ያባቶችህ ያይን ድንበር፣ ከተረከዘ ሎሚ ሳያልፍ
            አንተ ግን ጆቢራው-ዘራፍ
ጠፍር አይወስንህ ጉብል
ጥሎ በዘመንህ ዕድል
ዓይንህ ባት አልፎ እንዲዋልል፤
ቴህ ወዲያ ጀግንነት የለ፣ ተዚህ የከረረ ግዳጅ
ባደባባይ የዱር ገደል፣ ስትናደፍ የእግር አዋጅ
ሌሊቱን በየሌት- ‘ግለብ’፣ ቀኑን ጭምር በጠራራ

ሲነጋ እንደጧት ጆቢራ
በከተማህ ስታቅራራ
በዕድሜህ መንከራተት ሥራ፣
ካንዱ ቢሮ ሌላው ቢሮ፣ አቦል በረካውን ብለህ
ያገሩን ወሬ ተንትነህ
ተጨቃጭቀህ ተለፋልፈህ
አመሳጥረህ አቆላልፈህ፣ የዚያን ጉዳይ ከዚህ ጉዳይ
ዘጋግነህ በቡና ምገህ፣ አምተህ ደክመህ ስትለያይ፣
በዚህ ብቻ ሳታስቀረው፣ ደሞ አዲሱን የአገር ጠባይ
ከልማድ የቡና ሱስ ጋር፣ የዘመኑን ሳትለያይ
እስቲ ደሞ አራዳ ወጥተህ፣ በከተማው አደባባይ
ያንዷን ካንዷ ዳሌና ባት፣ እግሯን ከእግር ጋር አስተያይ!
ደርቶልህ ያገር ልጅ ቅልጥም
ዳሌው ባቷ እስኪፈረጥም
እየናረ እስኪያስገመግም
አንተ አድፍጠህ ከኋላዋ፣ በዓይንህ ሣግ ስታነፈንፍ
ያቺን ልክፍ ያቺን ንድፍ
እያረክ ስታሾልቅ፣ አንዷ ፈርታ አንዷ ስታፈጥ
ተጠግታህ ባቷ ሲያገምጥ
“ዘራፍ” ቀርቶ ቀልብህም “ውይ!”
እያለ ወኔህ እግር ይይ!
“በሠየጠኑትማ ዘንድ
አንዱም የባላንጣ ዘዴ፣ የባዕዳን ሥውር መንገድ
ዘመናጥ ጦር መሣሪያ ነው፣ ታዳጊ አገር ለማንጋደድ
እምነቱን ለማወናበድ
ያንድን ትውልድ የሕልም አቅጣጫ
ወደፊት ሳይሆን ወደታች፣ አመንምኖ ማቀጨጫ!”
ቢልህ ፈጥጦ በግልምጫ
ለኅሊናው ማጋለጫ
ናቀው እርግፍ አርገህ ተወው፣ ቴህ ቢጤው ጋር አትንጫጫ፡፡
ሠልጥነን ንቀን አልፈነው፣ የይሉኝታን መቀመጫ
የኛ ዓይን የእግር ነው እንጂ፣ በቅቶት ኅሊና መግለጫ፡፡
እርቀን ማስተዋል ማለት፣ የኛን ሥልጣኔ ድልድይ
እግር ማየት ነው ብለናል፣ አሜን በቃን እግር እንይ!
                               (ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን)
    ‘ለእግረተኞች’ – (፲፱፻፷፫ – ‘ፒያሳ’)
                                    እሳት ወይ አበባ

የዳኛቸው ወርቁ አጭር ልቦለዶች በፒ.ዲ.ፍ

የዳኛቸው ወርቁ
አጭር ልቦለዶች በፒ.ዲ.ፍ

ውድ የእልፍኜ ታዳሚዎቼ፣

ሠላምታዬ ባላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡ በዳኛቸው ወርቁ ተደርሶ በ 1962ዓ.ም የታተመው “አደፍርስ” መጽሐፍ ለአርባ ሦስት አመታት ያህል አነጋጋሪ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ በዚሁ ብሎግ ላይ ውስን ገጾችን በፒ.ዲ.ኤፍ እለቃለሁና ይከተሉኝ ፤ እስከዛው ድረሥ ግን 3 አጫጭር ልብ ወለድ እነሆ በረከት ብያለሁ፡፡
ሄ.ስ
ዳኛቸው ወርቁ በ፲፱፳፰ ዓ.ም. ደብረሲና ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በደብረሲና አጠናቀቁ:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ በ፲፱፶፫ ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም በማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የተቃውሞ ግጥሞችን ይጽፉ ነበር፡፡ ይህንንም በተመለከተ ስብስብ ሥራዎቻቸውን “እምቧ በሉ ሰዎች” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመዋል። 

ዳኛቸው ወርቁ
ዳኛቸው ወርቁ
1928-1987

ዳኛቸው ወርቁ በአዲስ ዘመንና በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ስለተለያዩ ጉዳዮች ይጽፉ ነበር፡፡ የተለያዩ ተውኔቶችን ጽፈዋል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንደምትቀላቀል በሚነገርበት ጊዜ “ያላቻ ጋብቻ ትርፉ ሐዘን ብቻ” የሚል ተውኔት ደርሰዋል፡፡ ከዳኛቸው ሥራዎች መካከል በ፲፱፷፪ ዓ.ም. ለኀትመት የበቃው “አደፍርስ” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ነው፡፡

በጊዜው የነበረውን የመኳንንቱንና የባላባቱን የአኗኑዋር ሁኔታ እንዲሁም ስለ ሃይማኖት በሰፊው ይገልጻል፡፡ “አደፍርስ” የታሪኩ ባለቤት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን ከአዲስ አበባ ወደ ባላገር በመሄድ በአንድ ላይ ቤት ተከራይተው መኖራቸውን በመተረክ በከተማውና በባላገሩ መካከል ያለውን ከፍተኛ የአስተሳሰብ፣ የልማድና የመሳሰሉትን ልዩነቶች በጉልህ ያሳያል፡፡/ምንጭ: የኢትዮዽያ ደራሲያን ማሀበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ።/

ከደራሲው ሥራዎች በከፊል
1. አደፍርስ(ልቦለድ)
2. እምቧ በሉ ሰዎች(ግጥምና ቅኔ)
3. አደፍርስ(ልቦለድ)
4. ሰቀቀንሽ እሳት(ተውኔት)
5. ሰው አለ ብዬ(ተውኔት)
6. ትበልጭ(ተውኔት)
7. ያላቻ ጋብቻ ፥ትርፉ ሐዘን ብቻ(ተውኔት)
8. ማሚቴ(ልቦለድ)
9.  የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት
10. የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት

11. ሰቀቀንሽ እሳት (የተሰኘ ተውኔት)
ለ ፒ.ዲ.ኤፍ ምንጬ፤
ምሥጋና ለየኢትዮጵያ ቤተመጻህፍት
ethiopianarchive.wordpress.com