የዳኛቸው ወርቁ አጭር ልቦለዶች በፒ.ዲ.ፍ

የዳኛቸው ወርቁ
አጭር ልቦለዶች በፒ.ዲ.ፍ

ውድ የእልፍኜ ታዳሚዎቼ፣

ሠላምታዬ ባላችሁበት ይድረሳችሁ፡፡ በዳኛቸው ወርቁ ተደርሶ በ 1962ዓ.ም የታተመው “አደፍርስ” መጽሐፍ ለአርባ ሦስት አመታት ያህል አነጋጋሪ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በቅርቡ በዚሁ ብሎግ ላይ ውስን ገጾችን በፒ.ዲ.ኤፍ እለቃለሁና ይከተሉኝ ፤ እስከዛው ድረሥ ግን 3 አጫጭር ልብ ወለድ እነሆ በረከት ብያለሁ፡፡
ሄ.ስ
ዳኛቸው ወርቁ በ፲፱፳፰ ዓ.ም. ደብረሲና ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በደብረሲና አጠናቀቁ:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡ በ፲፱፶፫ ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም በማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የተቃውሞ ግጥሞችን ይጽፉ ነበር፡፡ ይህንንም በተመለከተ ስብስብ ሥራዎቻቸውን “እምቧ በሉ ሰዎች” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትመዋል። 

ዳኛቸው ወርቁ
ዳኛቸው ወርቁ
1928-1987

ዳኛቸው ወርቁ በአዲስ ዘመንና በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ላይ ስለተለያዩ ጉዳዮች ይጽፉ ነበር፡፡ የተለያዩ ተውኔቶችን ጽፈዋል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንደምትቀላቀል በሚነገርበት ጊዜ “ያላቻ ጋብቻ ትርፉ ሐዘን ብቻ” የሚል ተውኔት ደርሰዋል፡፡ ከዳኛቸው ሥራዎች መካከል በ፲፱፷፪ ዓ.ም. ለኀትመት የበቃው “አደፍርስ” የተሰኘው መጽሐፋቸው በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ነው፡፡

በጊዜው የነበረውን የመኳንንቱንና የባላባቱን የአኗኑዋር ሁኔታ እንዲሁም ስለ ሃይማኖት በሰፊው ይገልጻል፡፡ “አደፍርስ” የታሪኩ ባለቤት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን ከአዲስ አበባ ወደ ባላገር በመሄድ በአንድ ላይ ቤት ተከራይተው መኖራቸውን በመተረክ በከተማውና በባላገሩ መካከል ያለውን ከፍተኛ የአስተሳሰብ፣ የልማድና የመሳሰሉትን ልዩነቶች በጉልህ ያሳያል፡፡/ምንጭ: የኢትዮዽያ ደራሲያን ማሀበር ለሚሊኒየም ያሳተመው አጀንዳ።/

ከደራሲው ሥራዎች በከፊል
1. አደፍርስ(ልቦለድ)
2. እምቧ በሉ ሰዎች(ግጥምና ቅኔ)
3. አደፍርስ(ልቦለድ)
4. ሰቀቀንሽ እሳት(ተውኔት)
5. ሰው አለ ብዬ(ተውኔት)
6. ትበልጭ(ተውኔት)
7. ያላቻ ጋብቻ ፥ትርፉ ሐዘን ብቻ(ተውኔት)
8. ማሚቴ(ልቦለድ)
9.  የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት
10. የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት

11. ሰቀቀንሽ እሳት (የተሰኘ ተውኔት)
ለ ፒ.ዲ.ኤፍ ምንጬ፤
ምሥጋና ለየኢትዮጵያ ቤተመጻህፍት
ethiopianarchive.wordpress.com

አደፍርስ – የብዕር ጠብታ

ሙሉውን ለማንበብ
ርዕስ  “አደፍርስ”

ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ

የታተመበት ዘመን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም

ቅንጣቢ ዳሰሳ  በሔኖክ ሥጦታው
ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ባስነበበን መዝገበ-ስብሐት “ማስታወሻ” መጽሐፍ ላይ ጋሼ ስብሐትን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-  “በአንተ የወጣትነት ጊዜ በአማርኛ ሃሳብን መግለፅ አይቻልም ብላችሁ አንተም ሆንክ ጓደኞችህ በእንግሊዝኛ መጻፍ የወሰናችሁበት ወቅት እንደነበረ ይነገራል። በኋላ ደግሞ ወደ አማርኛው ተመልሰህ ድንቅ ጸሐፊ ወጣህ። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ብትገልፅልኝ?”
ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፦ “በወጣትነቴ አማርኛ በምፈልገው መልኩ ሀሳብን መግለፅ አያስችልም የሚል እምነት ነበረኝ። በዚህም ላይ ያስተማሩን እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች መሆናቸውን አትርሣ። እኛ አናውቅም እንጂ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወጣቱን ትውልድ በቅኝ አገዛዝ ጥበባቸው ይዘውናል። በኋላ ዳኛቸው ወርቁ “አደፍርስን” ጻፈ። እኔ ሳነበው በአማርኛ መጻፍ እንደሚቻል ገባኝ። ስለዚህ በእንግሊዝኛ የመጻፍ ሀሳቤን ተውኩት። በወቅቱ አስታውሳለሁ “ሌቱም አይነጋልኝን” በእንግሊዘኛ መጻፍ ጀምሬው ነበር። . . .”
ማስታወሻ (ስብሐት ገብረእግዚአብሔር)ከዘነበ ወላ ፤ 1993 ዓ.ም የታተመ፤ ገጽ 238 
              ****** ******      ****** *****
 ጥቂት ስለ ዳኛቸው ወርቁ

ዳኛቸው ወርቁ «አደፍርስ» (፲፱፻፷፪ ዓ.ም.) በተሰኘ ልብ ወለድ ድርሰቱ. . . .ጭብጦች እና የተራቀቀ የአጻጻፍ ስልቱ የአማርኛን ዘመናዊ ልብ ወለድ ወደ ድንቅ ከፍ ካለ እርከን ያወጣ፥ «እምቧ በሉ ሰዎች» በሚለው የግጥም መድብሉ (፲፱፻፷፯ ዓ.ም.) ውስጥ በተካተቱ ግጥሞቹ ስለሀገሩ ልማትና ዕድገት ተቆርቋሪነቱን የገለጠ ዕውቅ የሥነ ጽሑፍ ምሁር፥ ሐያሲና ተርጓሚ የነበረ ሲሆን በልሳነ እንግልጣር(እንግሊዝኛ) በመጻፍም «The Thirteenth Sun» የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በዓለም አቀፉ መድረክ ካስተዋወቁ በጣት ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጸሓፍት አንዱ ነበር።” ይለዋል የአማርኛው ዊኪ ፒዲያ፡፡ሲቀጥልም፡-

“የፊውዳል ኢትዮጵያን ሶሲዮሎጂና የታሪክ ጥራዞች ከማንበብ፥ «አደፍርስ» ድርሰቱን ማንበብ ይቀላል’ የተባለለት ዳኛቸው ወርቁ የካቲት ፲፮ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ በይፋትና ጥሙጋ በደብረ ሲናከተማ አቅራቢያ ከአቶ ወርቁ በዛብህና ከወይዘሮ አሰገደች ሀብተወልድ ተወለደ። ከቤተ ሰቡ አምሥት ልጆች ዳኛቸው በኩር ነበር።…

የዛሬዎቹን ወጣት ኢትዮጵያውያን በጥበቡ ዘርፍ የሚታደጉ የሥነ ጽሑፍ ጥበብ መመሪያ፣ የአማርኛ ፈሊጦች መጽሐፍት ያሳተመ ምሁር ሲሆን አንድም ለሀገሪቱ ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውን «የማርክሲዝም ሌኒንዝም መዝገበ ቃላት» እና «የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት» የመሳሰሉ ጥልቅ እና ምጡቅ ሥራዎች ዝግጅት ላይ በመሳተፍ ምሁራዊ ግዴታውን የተወጣ ኢትዮጵያዊ ነበር።


“የሀገሩን እምነትና ባህል ጠንቅቆ የሚያውቅ፥ ለሥራ ነገን የማያውቅ፥ ለውጥ ፈላጊ፥ አገር ወዳድ፥ ስለሀገር ኋላ ቀርነት ሁሌ የሚቆረቆር ፥ ማጎብደድና ማቆሻበድ የማይወድ፥ ፊት ለፊት ተናጋሪ ባጠቃላይ በ«አደፍርስ» ልብ ወለድ ድርሰቱ ጠጣርና ምጡቅ ሐሳቦች በድንቅና ውብ የአጻጻፍ ስልት፥ ልዩ በሆነ የቋንቋ ኃይል የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ልዕልና ያሳየ – ዳኛቸው ወርቁ – በዚሁ ድርሰቱ የፈጠራ መጽሐፍ የሚነበብ ብቻ ሳይሆን ተደጋግሞ የሚነበብና የሚያወያይ መሆኑን – አዲስ ባህል የተከለ ብርቅ የጥበብ ሰው ነበር። . . .” በማለት የአማርኛው ዊኪ ፒዲያ መዝገበ-ሕይወቱን ያስነብበናል፡፡

              ****** ******      ****** *****


ስለ አደፍርስ ልብ ወለድ ድርሰት ሐምሌ(፲፱፻፱፫ ዓ.ም.) “አዲስ ርዕዮት” ጋዜጣ ላይ በጥበብ አምድ ስር “አደፍርስ – የብዕር ጠብታ”  በሚል ርእስ ቁንጽል ምልከታዬን እንዲህ አስነብቤ ነበር፡-

በ(፲፱፻፷፪ ዓ.ም.) ከታተሙ ሁለት የኢትዮጵያ ዘመናዊ  ሥነ-ጽሑፍ ፈር ቀዳጅ መጻህፍት ውስጥ አንዱ በዳኛቸው ወርቁ የተደረሰው አደፍርስ ሲሆን የድርሰቱን ዘመናዊ አቀራረብ ባልተረዱ አንቢያን ተቀባይነት አጥቶ እንደነበር ፀሓይ  የሞቀው እውነት ነው፡፡ በዚሁ ዓመት የታተመው ሌላው መጽሐፍ በበዓሉ ግርማ የተደረሰው “ከአድማስ ባሻገር” ነበር፡፡

የወቅቱ ማሕበረሰብ በአደፍርስ ውስጥ ነፍስ ዘርተው ሲንቀሳቀሱ ይታሉ፡፡ ወግ፣ ባሕል፣ እምነት፣ ሥነ-ልቦና . . .አብሯቸው ይተማል፡፡ ምዕራፋት የየራሳቸውን የብዕር ጠብታ እየፈነጠቁ ይጓዛሉ፡፡ ሕይወት ለአደፍርስ፣ ሕይወት በአደፍርስ ይገለጻል፡፡
ርዕሳችን የሆነው “አደፍርስ” በደራሲው ዳኛቸው ወርቁ አቀማመጥ ፣ “ጠይም ነው፣ ፊተ ሰልካካ፡፡ቀጭን ነው፣ ቁመተ ለግላጋ፡፡ሃያ አራተኛ ዓመቱን ይዟል – ከተወለደ፡፡” ለአለባበሱም ሆነ ለላይ ውበቱ ጭንቅ የለው፡፡ ባሰኘው መንገድ ይጓዛል፡፡ “ሞትና ሕይወት፣ ድንቁርናና እውቀት መፈራት የለባቸውም” የሚል ፈሊጥ አለው፡፡ “ልቡሰ ጥላ” የሚለው ቃልም ለአደፍርስ የእውነት መገለጫነት ትልቅ ቦታ አለው፡፡

“ልቡሰ ጥላ” ለአደፍርስ፣ መያዣ መጨበጫ የሌለው ምስቅልቅል ሁኔታ ነው፡፡ ከአዕምሮ ክፍሎች በአነስተኛው ውስጥ የሚገኝ ልዩልዩ ነገሮች ማየትና ማውጠንጠን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ የሚጠራቀም ነው-ይላል፡፡ልቡሰጥላ በተለያዩ መንገዶች የሚገኝ ውስጣዊ ግፊት ነው፡፡ የመፈለግ ፍላጎት፡፡ ከየዕለታዊ ተግባሮቻችን ከሚጠቅመንም ሆነ ከማይጠቅመን፣ ከመልካሙም ሆነ ከመጥፎው ፣ ለዓይናችን ከሚያስደስተንም ሆነ ከሚያስጠላን ሁሉ ወደ አዕምሯችን እየገባ የሚጠራቀም “ስሜት” ነው፡፡ እነግድህ ለአደፍርስ ልቡሰጥላ ይህን ትርጓሜ ይይዛል፡፡ 

ገጾች ሲገለጡ ፣ገፀ-ባህርያት ሲላወሱ፤ ሰዓሊው ክብረትን እናገኘዋለን፡፡ልዩ ባህርይን ተላብሷል፡፡ በሰዎችም ሆነ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሚመለከተው ውበትን ነው፡፡ የላይን ሳይሆን የውስጥን ገፅታ፡፡ደራሲው ዳኛቸው ወርቁ፣ ክብረት  በገዛ አንደበቱ ማንነቱን ያሳየናል፡፡ ገጸባህርያት በንግግራቸው ይለያሉ ፡፡ ንግግራቸው ድርጊታቸውን ይገልፀዋል፡፡ ክብረትም ይናገራል፤ ንግግሩ ሙያውን ያሳይበታል፡፡ አደፍርስ የክብረትን አስተሳሰብ ይጋራል፡፡ “ሰዓሊ ተግባሩ ውስጣዊውን ንቅናቄ አፍልቆ ማሳየት ነው መሆን ያለበት” ይለዋል፡፡ እርግጥ ሰዓሊው ክብረት  ወጣትን ሳይሆን ወጣትነትን ለመሳል በሚያደርገው ጉዞ የስሜቱ ተጋሪ አደፍርስ ብቻ ነው፡፡ እናም የዘወትር እውነታውን ሳይሆን ውስጣዊውን ሰብእና ሊደርስበት የሚሻው ሰዓሊው ክብረት አጋዥ አላጣም፡፡(በተቃራኒው በማሕበረሰቡ ልምድና ስርአት ጋር ለሚጋጨው አደፍርስ የደጋፊነት ሚና ይስተዋልበታል) ፡፡

ወ/ሮ አሰጋሽ በወቅቱ በነበረው የፊውዳል ስርአትን ወክለው የተቀረፁ የቀለም ጠብታ ውጤት ናቸው፡፡ህሊናዊ ገጽታቸውን ዘልቀን ለመመልከት የሚያስችሉ ድርጊቶች የመጽሐፉ አብይ አላማ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለአደፍርስ እንዲህ ሲሉት እንሰማለን፡-
“ከሰውም ሰው አለው፤ “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤ ከሰው መርጦ ለሹመት” ሲባል አልሰማህም የኔ ልጅ . . .አሁን ለምሳሌ አሽከሮቼን ገና ለገና በዝጌር አምሳል ተፈጥረዋል ብዬ ከኔ ጋር እኩል ናቸው ልል ነው? የለም የኔ ልጅ፣ ዙሪያውንም፣ አካባቢውንም እያዩ ነው ጨዋታ . . .” (ገፅ 101) ይሉታል፡፡ የወ/ሮ አሰጋሽን ሰብእና ለመረዳት ጥቂት ንግግራቸውን መስማት በቂ ነው፡፡ እዚህ ላይ ደራሲው ገፀባህሪያቱን በንግግራቸው እንዲለዩ የማድረግ ጥበቡን በመጽሐፉ ላይ በሰፊው ተጠቅሞበታል፡፡

 ለወ/ሮ አሰጋሽ የእኩልነት ጥያቄ ቦታ የለውም፡፡ሰው በፈጣሪ አምሳል መፈጠሩን ያምናሉ፤ መተቃራኒው ደግሞ ጌታና ሎሌ መኖሩን ያስረግጣሉ፡፡ “የአካባቢ ሕግ” ተከታይ ናቸውና፡፡ የአደፍርስ አመለካከት ለእርሳቸው የ“አይነጥላ” ውጤት ነው፡፡ ለዚህም “አባዜ” መፍትሄ ስራይ  “የድንገተኛ” ቅጠል ብጠሳ ይጓዛሉ፡፡ “ድንገተኛ ይፈውሰው ይሆን?”ን እያሰላሰሉ፡፡

አደፍርስ የዘመን አሻራ ነው፡፡ ልክ እንደሱው ሁሉ ሌሎች ደራሲያንም በቀረጹት ገፀባህሪያት የዘመኑን አሻራ አትመው አኑረውልናል፡፡ “ፍቅር እስከ መቃብር” በጉዱ ካሳ፤ “አደፍርስ”-በአደፍርስ፣ “ከአድማስ ባሻገር”-በኃይለማርያም፤ “ሀዲስ”-በሀዲስ፡፡በበዓሉ ግርማ የተደረሰው “ሀዲስ” ልብወለድ መጽሐፍ፣ ከወግ እና ባህል ጋር የሚጣረሰው አደፍርስ ጋር ተወራራሽ ባህርይ ይስተዋልበታል፡፡ አደፍርስ እና ሀዲስ የትላንቱን፣ የዛሬውንና የነገን ድርጊቶች አንግበው ሲጓዙ ይታያል፡፡በተመሳሳይ መልኩ የፍቅር እስከመቃብሩ ገፀባህርይ ካሳ ዳምጤ(ጉዱ ካሳ)፣ በአደፍርስ ምስለ-ባህርይ ውስጥ ይታያል፡፡ከአድማስ ባሻገሩ ኃይለማርያም የአደፍርስን ሰብእና ሲገለጥ የሚታይ ሌላ ባህርይ ነው፡፡ /ተወራራሽ ባህሪያትን በሌላ ርዕስ በሰፊው እመለስበታለሁ/፡፡

አደፍርስ የብዕር ጠብታ ነው፡፡ ከልማድ እና ስርአት ጋር አንገት ለአንገት እንደተናነቀው ሁሉ፣ ከእምነት ጋር ግብግብ ገጥሟል፤ “ለሠይጣን መስዋእት የታረደን በግ የበላ ሰው ይቀሰፋል” የሚል እሳቤ ተብትቦ በያዘው ማህበረሰብ ውስጥ ህብረ-ጥምሮሽ ጎልብቶ እውነታው ፈጥጦ ሲወጣ፤ “እንቢ በል አንተ ሰው!” እያለ በሽለላ አስተጋብቷል፡፡
ይቀጥላል›››››››››

ሙሉውን ለማንበብ