እስረኞቹን ፍቺ !

እኔ ዛሬ ምኒልክን ስለምን አደንቀዋለሁ ?
ከቶ ለምን አብዲስ አጋን – ጐበናን አወድሳለሁ ?
ስለምን ገረሱ ዱኪን – ካዎ ጦናን አነሳለሁ ?
ከእንግዲህ ለአያ በላይም – ለቋረኛውም አልዘፍንም
ለሰሜኑ ልጅ አሉላ ያማረ ቅኔ አልቀኝም
ኃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ በእርስዎ  ስምም አልፎክርም
እኔ የገብርዬ ባርያ! የአባ ጅፋር ልጅ አልልም !!
አልልም! ከቶም! አልልም!
አይኔን ወደፊት ነው እንጂ ወደኃላዬስ አልጥልም!!
ከእንግዲህ ኩራት ፍለጋ አልሄድም ወደትላንቱ
ከገዛ ትውልዴ መሀል ተገኝታለች አንዲት ‘ብርቱ’
       ለምን ወደኃላ ሄጄ ሙታን እቀሰቅሳለሁ?
       አዲስ ኮከብ  ስትወለድ በአይኔ ብረቱ አይቼአለሁ!!
       ዛሬማ ልቤን ሞልቼ ፣
       ዛሬማ ታሪክ አይቼ ፣
       የግንቦት ጭጋግ ደመናን፣ ጨለማን የተቃወመች
       ይኸው አዲስ አበባ ላይ አዲስ ኮከብ ተወለደች
       ሎሚ መቼም መድሃኒት ነው፣ ማንጐም – ትርጐም ደስ ይላል
       ግና ከፖም – ከመንደሪን ብርቱካንን ያህል የታል ?
       የታል? የታል? የታል? የታል?
       ከስንቱ ጥሬና ብስል ብርቱካንን ያህል የታል?

       ለእምነቷ ሟች – ትሁት ምሁር
       የሴት ጀግና – የሴት ነብር
       ብልህ ናት እንደጣይቱ ሀሞት – ወኔዋ የሰላ
       አንደበቷ የጣፈጠ  ልቧ እውነትን የተሞላ
       “የቃሊቲውን ጨለማ እስር ቤቱን እፈራለሁ
       ሆኖም እውነት ከሚጠፋ መታሰርን እመርጣለሁ “
        አለች – አሉ ይቺ ጀግና
        ልበ ሙሉ – ልበ ቀና
               እባክሽን አንቺ ሴት ሆይ! በይ መላውን  አሳያቸው
               “ምርኮ አገባን” እንዳይሉ ይኸው ታስረሽ – አሰርሻቸው
               ምን ታምር ነው የአንቺ ስራ? እውነት ምንድነው ሚስጥሩ?
              “መንፈስ ሆነናል” እንዳልሽው አስራለሁ ያሉት ታሰሩ
               ፍቻቸው! በያ ፍቻቸው!
               ከዚህ ክፉ የእግር ብረት ከዚህ ክፉ ካቴናቸው
               ፍቻቸው! እቴ ፍቻቸው!
               ከሆድ እቃ በተረፈ ልበ ፍቅር የሌላቸው
               ክፉ ቅዠት የተሞሉ ሕልም ግን የጎደላቸው
               ፍቻቸው! አንችው ፍቻቸው!
               እስረኞቹ እነሱ ናቸው፡፡
               ጨለማው ብርሃን ሆኖ ብርሃኑ ጨለማቸው
              
               “አንድነት” ያልሽው መድሃኒት በሽታ የሆነባቸው
               ብረት መሸከም ነው እንጂ ዘንባባ የማይገባቸው
               ፍቻቸው! አንችው ፍቻቸው!
               “አይን እያላቸው አያዩም” የተባሉት እኚህ  ናቸው
               የማይሰሙ – የማይለሙ ትላልቅ ጆሮ እያላቸው
               ምላሳቸው ግን የፋፋ
               በካይ መርዝን የሚተፋ
               ፅድቁን – መልካሙን አንኳሳሽ
               ጥንቡን – እርኩሱን አወዳሽ
               ያጐረሳቸውን ነካሽ
               ሰናይ ምግባር የሸሻቸው
               ህዝበ – ፍቅር የራቃቸው  
               ልበ – ሰላም የሌላቸው
               ፍቻቸው! እቴ ፍቻቸው!
               እስረኞቹ እነሱ ናቸው፡፡
    
     ደበበ የመድረኩ ፈርጥ ለክብርሽ እንደተቀኘው
     መልዐክ ስምሽን አውጥቶት “ብርቱ – ካህን” ነሽ እንዳለው
     ፍቻቸው! በያ ፍቻቸው!
     በቀን እንደማይወጣ ጅብ በጨለማ ነው ኑሯቸው
     ፍቻቸው! እቴ ፍቻቸው !
     ከንስሃ ጋር እንዲሆን አይቀሬ ሞት ፍጻሜያቸው
     ፍቻቸው! አንችው ፍቻቸው!
     እስረኞቹ እነሱ ናቸው፡፡     
    
  ተጻፈ፡- ጥር 2003 ዓ.ም
በሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) ከፀሐይ በታች መድብል 2004ዓ.ም 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s