** ባይገርምሽ 10 ** የ-ዮሐንስ ሞላ ግጥም

** ባይገርምሽ 10 ** 

ባለፈው ‘ረክቼ፣ መጪውን አልሜ፣ 

ተንብዬ፣ ቋምጬ፣ ስዬው ተደምሜ፣ 

በተስፋ የተገራ፣ አምባላይ ተጭኜ፣ 

ወደ ፊት ሽም’ጬ፣ መሪዬን ታምኜ፣ 

አንቺን ተደግፌ፣ ካንቺ ጋር ኳትኜ፣ 
የዓለሙን ግሳንግስ
… ትርምሱን ንቄ፣ በሀሳቤ መንኜ፣ 
ፍቅር ገዳም ሄጄ፣ ከጊዜ ቀድሜ፣ 
ካንቺ ጋር ቆርቤ፣ ካንቺ ጋር ገድሜ፣ 
ከተራራው አናት፣ ከአምባው ላይ ሰፍሬ፣ 
ኮረብታው ጫፍ ውዬ፣ በምናብ በርሬ፣ 
ጢንቢራዬ ዞሮ፣ በፍቅርሽ ሰክሬ፣
ባንቺ ስንገዳገድ…ላንቺ ስወላገድ፣ 
በተስፋ፣ በኩራት፣ ስወድሽ የኔ ውድ…
እህህህ… ግን ያልፋል ዓለሜ!

ማንም ከማያውቀው ከኔና አንቺ በቀር፣ 

ከደብራችን አፀድ፣ ከቃላችን መንበር፣ 

ስኳትን ስዳክር…ሰላሜን አሰሳ፣ 

ደስታዬን ፍለጋ፣ ስወድቅ ስነሳ፣ 

ደስታና ሰላሜን፣ ጠምረሽ ሸክፈሽ፣ 

ውዴ አንቺን ስወድሽ…

በንቃት ስወድሽ፣ ልቤ ላንቺ ደክሞ፣ 

ኤጭ!… ይህም ያልፋል ደግሞ!

ደጋግሞ ሲጥለኝ፣ ፍቅርሽ አደናቅፎ፣ 

ስነሳ ሲጥለኝ፣ መውደድሽ ጠላልፎ፣ 

ድጋሚ ሲጥለኝ…ቀልቤ እየታወከ፣ 

በናፍቆት እንቅፋት፣…

….ጉልበቴ እየራደ፣ ልቤ እየበረከ፣ 

በትዝታ ጥፍር፣ ውስጤ እየታከከ፣ 

ደስ እያለኝ ውዬ…

ግን እርሱም አለፈ! መከነ እንደጤዛ፣ 

ከቅዠቴ ዓለም፣ ብንን ስል ተረሳ፣ 

ግን እንኳን አለፈ…!

በሚጨበጥ ጉጉት፣ ይበልጥ በሚያፈካ፣ 

እልፍ በሚረቅ’ ስሜት፣ በሌላ ተተካ፣ 

ከጎኔ ሳገኝሽ… ውዴ አንቺን ስወድሽ፣ 

ግና…. ዝንቱሰ ውእቱ ይአልፍ!

በፍቅርሽ ናውዤ፣ በናፍቆት ታምሜ፣ 

ከአጠገቤ እያለሽ፣ በጭንቀት ደክሜ፣ 

ልደርስ፣ ልነካሽ፣ ስፍጨረጨር ቆሜ፣ 

ጮኬ፣ አቃስቼ፣ በጣር ተስለምልሜ፣ 

እንደ ጅል ስዳክር፣ ተወሳስቦ ዓለሜ፣ 

ውዴ አንቺን ስወድሽ…

ደስ በሚል ህማም…ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ 

ዝንቱሰ አላፊ ውእቱ!

ላፍታ ሳጣሽ ደግሞ፣ ውይ ስታስጨንቂ፣ 

መንገድ ከማቅናትሽ፣ ከሰማይ ስትርቂ፣ 

ስታፈላስፊኝ፣ ስታስለፈልፊኝ፣ 

….ስታስቀባጥሪኝ፣ ከአድማሱ ስትረቅቂ፣ 

ከአድማሴ ተተክለሽ፣ ስታንፀባርቂ፣ 

መምጣትሽን ባለምኩ፣ ‘አለች…’ ባልኩኝ ብቻ… 

በደስታ ሰፈካ፣ ‘ርካቡን ስረግጥ፣ የልቤን ኮርቻ፣ 

ቀኔን ስትባርኪው፣ ልቤን ስታደምቂ፣ 

ስታብለጨልጪ፣ ቤቴን ስታሞቂ፣ 

ስታንቆላልጪያት፣ ፀሀይን ስታስንቂ፣ 

ከወርቅ እንቁ ልቀሽ፣ ስታብረቀርቂ፣ 

ግን እሱም ያልፋል ዓለሜ፣ 

ግን እኔ ስወድሽ…

በኩራት፣ በአግራሞት፣ በፍዘት፣ ስወድሽ…

ዝንቱሰ አላፊ ውእቱ! 

በሚበልጥ ስሜት፣ መንፈሴ ሲረካ፣ 

ሺ በሚልቅ ኩራት፣ በሌላ ሲተካ፣ 

ዝም ብዬ ስወድሽ…ስወድሽ…ስወድሽ….

ኸረ ስንቱ አለፈ… 

ናፍቆት ጥበቃዬም፣ እንኳን ሌላው ቀርቶ፣ 

በመድረስሽ ዜና፣ ልቤ ዳግም ሞልቶ፣ 

ውዴ አንቺን ስወድሽ…

ወይ ጉድ…. ዝም ብዬ ስወድሽ፣ 

ስንቱ ተዳበለ፣ ስንቱ ተቀረፈ?!

ስንቱ ተበራታ፣ ስንቱ ተሳነፈ?!

ስንቱ ተገናኝ፣ ስንቱ ተላለፈ?!

ስንቱ ፍቅር ሞቀ፣ ስንቱ ቀዘቀዘ?! 

ስንቱ ተወዳጀ፣ ስንቱስ ተላዘዘ?!

ኸረ ስንቱ መጣ፣ ኸረ ስንቱ ሄደ?! 

ስንቱ ጉድ ታለፈ፣ ስንቱ ጉድ ነጎደ?!…

ውዴ አንቺን ስወድሽ…

እንደ ብዙ ነገር እንዳዲስ እንዳዲስ…

ስወድሽ…ስወድሽ… ስወድሽ…

ስንት ዓለም አለፈኝ…?!

ግን ምን አይተሸ ውዴ? 

ገና ስንቱ ያልፋል፣ ሰማይና ምድሩ፣ 

ፀሀይና ጨረቃ፣ ከዋክብት ጠፈሩ፣ 

ኩሉ ይአልፍ ዓለሜ!

ዝም ብዬ ስወድሽ፣ እያልኩ ማራናታ፣ 

ቀኑ እስከሚደርስ፣ አምላክ እስኪመጣ….

ስወድሽ….ስወድሽ….ስወድሽ….

/ዮሐንስ ሞላ/

https://www.facebook.com/lijalem

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s